"የአገር ውስጥ የጥራጥሬና ቅባት እህል ዋጋ መወደድ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳንሆን እያደረገን ነው" - ላኪዎች

101
አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ የጥራጥሬና ቅባት እህል የሚሸጥበት ዋጋ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ ላኪዎች ተናገሩ። ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በስብሰባው የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ላኪዎች ለኢዜአ እንዳሉት ወደተለያዩ የአለም አገራት የግብርና ምርቶችን ለመላክ ከአገር ውስጥ የሚገዙበት ዋጋ ከፍተኛ መሆን በአለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸው ላይ ጫና ፈጥሯል። ሰሊጥና ጥራጥሬ ወደተለያዩ አገሮች የሚልኩት አቶ ይትባረክ ዘገየ ኩባንያቸው በ2010 ዓ.ም ወደውጭ ከላከው የሰሊጥ ምርት ብቻ 17 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች በአገር ውስጥ የሚገዛበት ዋጋ በአለም ገበያ ከሚሸጥበት ጭማሪ ማሳየቱ በሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በመሆኑም የጥራጥሬና ቅባት እህል በአገር ውስጥ የሚቀርብበት ዋጋ ምክንያታዊና ከአለም አቀፉ ገበያ ጋር የተጣጣመ የሚሆንበትን መንገድ እንዲቀይስ አቶ ይትባረክ ጠይቀዋል። መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ከሆነ አገሪቱ ከጥራጥሬና ቅባት እህል የወጪ ንግድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደምትችልም ነው የገለፁት። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ካሳ ይትባረክ በበኩላቸው ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ለአለም ገበያ እያቀረቡ ሲሆን በአመት የሚያስገቡት የውጭ ምንዛሬ ከ4 ሚሊዮን ዶላር የዘለለ አይደለም። "ለዚህም ምክንያቱ በአገር ውስጥ ምርቶቹ የሚቀርቡበት ዋጋ ውድ ነው፤ ይህም በዓለም ገበያ በቂ ምርት እንዳናቀርብ እያደረገን መሆኑ ነው" ብለዋል። ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱ ከገበያ እስከመውጣት የሚደርስ ችግር ሊገጥማት እንደሚችልም ነው ባለኃብቱ የተናገሩት። የአምባሰል ንግድ ስራዎች ሃላፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አዲስ መካሻ በበኩላቸው የግብርና ምርቶችን ከአለም ዋጋ ጋር በተመጣጣኝ ዋጋ አለማግኘትን ጨምሮ የገበያ መዳረሻ ላይም ክፍተት እንዳለ ገልፀዋል። በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ጀነራል ዳሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ ጉዳዩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አጠቃላይ የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም መካከል ከአገር ውስጥና ከአለም ገበያ ዋጋ የሚስተዋለውን የዋጋ አለመጣጣም ማስተካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ መዳረሻ አገሮች 145 ደርሰዋል። የአመለካከትና የመዋቅር ችግር የኢትዮጵያን ምርት ለአለም አገራት የማስተዋወቅና ገበያ የማስፋት ተግባር በተፈለገው መጠን እንዳይሰራ አድርጎት ቆይቷል ይላሉ። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው እሴት ጨምረው ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሃብቶችን መንግስት ይደግፋል ብለዋል። እንደሚኒስትሯ ገለጻ በግብርናው ዘርፍ ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ፣ ገበያ ተኮር የግብርና ስራና ዘመናዊ ገበያን ማስፋት በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች መሆናቸውን ገልጸው ከዋጋና ተያያዥ ችግሮችም በዛው የሚፈቱ ይሆናል። ዛሬ በተጀመረው ስምንተኛው አለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ስብሰባ ከ140 ከአለም አገሮች የመጡ ገዥዎችን ጨምሮ የቅባትና ጥራጥሬ አቀነባባሪዎችና ላኪዎች አጠቃላይ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በጉባኤው ዘርፉን የተመለከቱ ጹህፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግ ሲሆን የአገር ውስጥ አቀነባባሪዎችና ላኪዎች ከአለም አገራት ከመጡ ገዥዎች ጋር ትስስር ይፈጥራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ነገ ይጠናቀቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም