በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ለ1 ሺህ 100 ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ተሰጠ

87
    አርባ ምንጭ ሚያዝያ 25/2010 “ሂማሊያን ካትራክት” የተሰኘ የአሜሪካን ግብረ ሰናይ ፕሮጀክት ላለፉት ሰባት ቀናት በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ለ1 ሺህ 100 ሰዎች  የነጻ  የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ  ህክምናና የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ኑሩ ኢብራሂም በሰጡት አስተያየት በዓይን ብሌን ጠባሳ ችግር ምክንያት ከልጅነታቸው ጀምሮ ህመም ሲሰማቸው መቆየቱንና ከ3 ዓመት ወዲህ ሙሉ በሙሉ ማየት እንደተሳናቸው ተናግረዋል ፡፡ በሆስፒታሉ ከአሜሪካን በመጡ የዓይን ህክምና ባለሙያዎች በተደረገላቸው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና ዳግም ማየት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡ ''ብርሃኔ ዳግም በመመለሱና ሠርቼ ቤተሰቤን ለማስተዳደር በመብቃቴ ደስታዬ ወደር የለውም'' ሲሉም ገልጸዋል  ፡፡ በተመሳሳይ ከያቤሎ የ2 ዓመት ልጃቸውን ያሳከሙት አቶ ቦሩ ጃሮ በበኩላቸው ልጃቸው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ማየት እንደማይችል ተናግረዋል ፡፡ በተደረገው ነፃ ህክምና ልጃቸው ማየት በመቻሉ ደስታቸው ወደር እንደሌለው  ጠቅሰዋል፡፡ ''ገና ህፃን እያለሁ በአግባቡ ማየት ባለመቻሌ ምክንያት ወላጆቼ በባህላዊ መንገድ ያደረጉልኝን እገዛ ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ማየት ተስኖኝ ነበር'' ያለችው በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የ20 ዓመት ወጣት ትዕግስት በቀለ ናት ፡፡ ''በተደረገልኝ ህክምና አሁን ሰዎችንና አከባቢዬን ለማየት በመታደሌ ዳግም የተወለድኩ ያህል ተሰምቶኛል'' ብላለች፡፡ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የዓይን ክፍል ኃላፊና ስፔሻሊስት ዶክተር ዳዊት ግዴይ  “ሂማሊያን ካታራክት” የተሰኘ ግብረ -ሰናይ ድርጅት ባደረገው ነፃ የዓይን ህክምና 1ሺህ 100 ወገኖች ብርሃናቸውን መመለስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 7ቱ የዓይን ብሌን ጠባሳ ችግር ያለባቸው በመሆኑ የብሌን ንቅለ ተከላ ተካሄዶላቸዋል፡፡ በሆስፒታሉ የ”ሂማሊያን ካትራክት ፕሮጀክት“ አስተባባሪ አቶ ደመቀ ደበበ በበኩላቸው በኢኮኖሚም ሆነ በባለሙያ ችግር በርካታ ዜጎች መዳን እየቻሉ የዓይን ብርሃናቸውን እንደሚያጡ ጠቅሰዋል፡፡ በሆስፒታሉ የተደረገው ነፃ ህክምና 10 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትና ውጤታማ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም