የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ወይዘሪት ብርቱካን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገለጹ

62
ጅማ ህዳር 14/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መምረጡ እንዳስደሰታቸው የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ምክር ቤቱ የሕግ ዕውቀትና የዴሞክራሲ ባህል ልምድ ያላቸውን ግለሰብ በሰብሳቢነት መምረጡ አርክቷቸዋል። ሐጂ ሱልጣን ዑመር የተባሉት ነዋሪ የምክር ቤቱ አባላት ነፃና ዴሞክራሲ አካሄድን በተከተለ መንገድ ወይዘሪት ብርቱካንን ምርጫ ለሚያስፈጽመው አካል ሰብሳቢነት መምረጣቸው ተገቢ ሆኖ አንዳገኙት ተናግረዋል። ተሿሚዋ በአገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ሲታገሉና ሲያታግሉ መቆየታቸው አሁን የተመደቡበትን ሥራ በብቃት ለመወጣት እንደሚያስችላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።ለሥራቸው  ስኬታማነትም ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል። ተሿሚዋ በቀጣይ በአገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች ነፃ፣ ተዓማኒና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እንደሚሆኑ አምናለሁ ሲሉም ተናግረዋል። የጅሬን ቀበሌ  ነዋሪ ወጣት አይሻ ጀሃድ በበኩሏ የምክር ቤቱ አባላት ያደረጉት ውይይት የተመሯጯን ማንነት በቀላሉ ለማወቅ አስችሎኛል ትላለች። ወይዘሪት ብርቱኳን በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የነበራቸው እንቅስቃሴ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያስችላቸዋል ስትል እምነቷን ገልጻለች። በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪው ተካልኝ ታደሰ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሿሚዋን ያቀረቡበትና የምክር ቤቱ አባላት የተቀበሉበት ሁኔታ የአገሪቱን ሕዝቦች ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብሏል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በአራት ተቃውሞ፣ በሦስት ድምፀ ተዓቅቦና  በአብላጫ ድምፅ ሾሟል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም