የጎርጎራ የዓሣ ምርምር ማዕከል ዳግም ሊከፈት ነው

1889

ጎንደር ህዳር 14/2011 በጣና ሐይቅ ብዝሃ ሕይወት ጥናትና ምርምር የሚያደርገው የጎርጎራ የዓሣ ምርምር ማዕከል ዳግም ተከፍቶ አገልግሎት ሊጀምር ነው።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እንስሳት ሃብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ይበልጣል ተረፈ ለኢዜአ እንደተናገሩት ማዕከሉ በዚህ ዓመት አጋማሽ ሥራ የሚጀምረው የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በደረሱት ስምምነት መሠረት ነው።

ላለፉት ሰባት ዓመታት አገልግሎቱን አቋርጦ የነበረውን ማዕከል ወደ ሥራ ለማስገባት ሚኒስቴሩ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ይሰጣል።

ሦስት ተመራማሪዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም ተመድበውለታል ብለዋል።

ማዕከሉ የሐይቁን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅና ለማልማት የሚያስችሉ ጥናቶችና  ምርምሮችን እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሐይቁ ዓሣ ለአካባቢው ኅብረተሰብና ብሎም ለክልሉ ጥቅም የሚሰጥበትን መንገድ በማመቻቸት የምርምር ሃሳቦችን በማፍለቅ ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚቀርብ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

ማዕከሉ ለባለሙያዎች፣ ለዓሣ አስጋሪዎችና አርቢዎች የስልጠና ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል፡፡

በማእከሉ በሚያቋቁማቸው የዓሣ ማራቢያ ገንዳዎች አማካኝነት ጫጩቶችን በማራባት ወደ ሐይቁ እንደሚያስገባም ዶክተር ይበልጣል አስታውቀዋል።

በዞኑ በግላቸው የዓሣ ኩሬ በማዘጋጀት በልማቱ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችም ምርታማ ዝርያዎች ይቀርቡላቸዋል ብለዋል፡፡

የማዕከሉ ዳግም መከፈት የዞኑ ዓሣ አርቢዎች ከባህር ዳር የዓሣ ምርምር ማዕከል ጫጩቶችን ለማምጣት ይገጥማቸው የነበረውን የጊዜና የገንዘብ ብክነት እንደሚያስቀርላቸውም ገልጸዋል፡፡

በጎርጎራ ወደብ አጠገብ የሚገኘው ማዕከል የተመራማሪዎች መኖሪያና መሥሪያ ቦታዎችን ጨምሮ የሰልጣኞች ማደሪያ፣ መማሪያና  መመገቢያ ክፍሎች አሉት፡፡