በአዳሚ ቱሉ ወረዳ በተሽከርካሪ አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ

52
አዳማ ህዳር 14/2011 በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ትናንት ምሽት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኝነት ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ከአርሲ ነገሌ ከተማ 27 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ቡልቡላ ከተማ ሲጓዘ የነበረ ኮድ 3 -41772 ኦ.ሮ የሆነ አይሱዙ የህዝብ ማመላለሻ ስድስት ሰዎችን አሳፍሮ በተቃራኒ አቅጣጫ ሲጓዝ ከነበረ ባለሶስት እግር ባጃጅ ጋር በመጋጨቱ ነው። በአደጋው በባለሶስት እግር በባጅ ውስጥ የነበሩ ስድስት ሰዎችና ሁለት እግረኞች ወዲያውኑ ህይወታቸው ማለፉን ኮማንደሩ ተናግረዋል። አደጋውን ያደረሰው አይሱዙ የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪና ረዳቱ ለባቱ ከተማ ፖሊስ እጃቸውን ሰጥተዋል። የሟቾቹች አስከሬን በባቱ ሆስፒታል  ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ለቤተሰቦቻቸው መስጠቱን ኮማንደር አስቻለው ተናግረዋል። "አይሱዙ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ከመጠን በላይ በሆነ ፍጥነት ደርቦ ለማለፍ በመፈለጉ ምክንያት አደጋው ደርሷል" ብለዋል። ባለሶስት እግር ባጃጅ ሶስት ሰዎች ብቻ መጫን ሲገባው ከመጠን በላይ መጫኑም ተገቢ እንዳልነበረ ኮማንደር አብራርተዋል። አሽከርካሪዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ህግና ደንብ በማክበር በሰውና ንበረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በመከላከል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኮማንደር አስቻለው መልእክት አስተላልፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም