በትምህርት ተደራሽነት የተገኘውን ውጤት በጥራት መድገም ይገባል - የዘርፉ ባለሞያዎች

72
ድሬዳዋ ግንቦት16/ 2010 በትምህርት ተደራሽነት የተገኘውን ውጤት በጥራት በመደግም የሀገሪቱን ራዕይ ማሳካት  እንደሚገባ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ገለፁ፡፡ ምሁራኑ ይህን የተናገሩት የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ከአምስት የሀገሪቱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥናት፣ በምርምርና በሃብት አጠቃቀም ጉዳዮች ላይ በጋራ  ለመስራት ድሬዳዋ ላይ በመከሩበት ወቅት ነው፡፡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሀረማያ፣ የአዲስ አበባና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደገለፁት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተስፋፍተዋል ። "አገልግሎቱ ተደራሽ በመሆኑ ዜጎች በሚኖሩበት ስፍራ ፍትሃዊ የትምህርት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል" ብለዋል ። እንደ ሙሁራኑ ገለጻ  በዘርፉ የተመዘገበው ስኬት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍና ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው፡፡ በትምህርት ተደራሽነት ላይ የተገኘው ውጤት በትምህርት ጥራት ላይ በመድግም የተሻሉ ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራት የሀገሪቱን ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ለተግባራዊነቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ መጀመሪያ ደረጃ ትምህረት ቤቶች፣የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተናጠልና የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የገጠር ልማት ኤክስቴንሽን መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሙሉቀን ገዛኻኝ  በሰጡት አስተያየት ባለፉት 27 ዓመታት በትውልድ  አካባቢያቸው ትምህርት እስከ መንደር መስፋፋቱን ጠቁመዋል፡፡ እሳቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ በአካባቢያቸው ብቸኛ እንደነበሩ  አስታውሰው አሁን ግን በአካባቢያቸው ጭምር  ዩኒቨርሲቲ መከፈቱ ለተማሪዎች አማራጭ ዕድል የፈጠረና ብዛት ያለው የተማረ ትውልድ ለማፍራት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ ''እነዚህን ውጤቶች በጥራትም በመድገም፣ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት  ከታችኛው ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ የምንገኝ ምሁራን ያሉብንን ክፍተቶች መፍታት ይገባናል'' ብለዋል፡፡ በየደረጃው የሚቀረፁ ስርአተ ትምህርቶች በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ የገበያ መስኮችን ከግምት ያስገቡ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል ። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር አጋርነት ዳይሬክተር ዶክተር ነጋ አሰፋ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በመላው የሀገሪቱ ትምህርትን በእኩል ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ''በተደራሽነት የተገኘውን ውጤት በጥራት ለመድገም ምሁራን ጥረት ማድረግ ይገባናል'' ብለዋል ። የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር መሐመድ ኑር አህመድ በበኩላቸው ''የትምህርት ጥራት በአንድ ጊዜ የሚመጣ ሣይሆን ከወላጆች  እስከ ትምህርት ሚኒስቴር  ያሉ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ሌት ተቀን መስራትን ይጠይቃል'' ብለዋል፡፡ የመምህራንን አቅም መገንባትና የኑሮ ደረጃን ማሻሻልም ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እየተዘጋጀ የሚገኘው ፍኖተ ካርታ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመላክተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ባለሙያ አቶ እዮብ አስፋው ''የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የትምህርት ክፍሎች አመራሮች ከሹመት ይልቅ በብቃትና በችሎታ ቢደለደሉ በዘርፉ የተሻለ ጥራት ለማምጣት ያስችላል '' ብለዋል፡፡ ለምርምርና ጥናት ከፍተኛ በጀት መመደብ ለጥራት መረጋገጥ ይበልጥ አስተዋፆ እንዳለው ባለሞያው አስታውቀዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም