በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈታ በቅንጅት እየተሰራ ነው - የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር

98
አሶሳ ህዳር 13/2011 በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈቶ የመማር ማስተማር ስራው በአፋጣኝ እንዲጀመር የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለፁ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን በመግለጫቸው በሰሞኑ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በጠፋው የተማሪዎች ህይወት የክልሉ መንግስት በእጅጉ አዝኗል፡፡ ተማሪዎች የራሳቸውን፣ የቤተሰብንና የመንግስትን ጥረት ከዳር እንዲደርስ እኩይ አላማ ያላቸው አካላት ማስፈጸሚያ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል፡፡ ግጭቱ በአጭር ጊዜ ተፈትቶ የመማር ማስተማር ሥራው በአፋጣኝ እንዲጀመር የፌዴራልና የክልል ተወካዮች ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚገቡ ጠቅሰዋል፡፡ ጉዳዮን በሃገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የከተማ ነዋሪዎችና መንግስታዊ ተቋማት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በካማሽ ዞን የተከሰተው ግጭት ባለፉት አራት ወራት በክልሉ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል፡፡ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልልና ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በክልሉ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ  እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደሩን አስረድተዋል፡፡ "የክልሉ አመራር ሃገራዊ ለውጡን አልተቀበለውም” በሚል በተለያዩ አካላት የሚነሳው ሃሳብ ትክክል አለመሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ  "ከየትኛውም አካባቢ ቀድመን የአመራር ለውጥ በማድረግ በተግባር ለውጡን ደግፈን እየሰራን ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ አሶሳ፣ ቶንጎ፣ ሸርቆሌ እና ሌሎችም አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡ በካማሽ ዞን ተከስቶ ከነበረው ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ  በመንገድ እጦት ምክንያት  የወንጀል ምርመራ ስራ አለመጀመሩን የገለጹት አቶ አሻድሊ በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ''በክልሉ በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ግጭቶች ዋነኛው ምክንያት የመልካም አስተዳደር እጦት ነው''  ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግስትና ገዢው ፓርቲ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮችን ቁመና ፈትሾ ማስተካከያ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉን አመራሮች  የመፈተሸ ስራው የዘገየው በክልሉ ያለውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ በመቆየቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በቀጣይ የክልሉ መንግስት አሰራሩን ለህዝቡ ግልጽ የማድረግ አካሄድ እንደሚከተል አቶ አሻድሊ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም