ምክር ቤቱ ወይዘሪት ብረቱካንን መሾሙ ቀጣዩ ምርጫ ታማኝና ፍትሃዊ ይሆናል የሚል እምነት አለን-ምሁራን

143
ደብረ ብርሀን ህዳር 13/2011 "የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መሾሙ ቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ ታማኝና ፍትሃዊ ይሆናል የሚል እምነት አለን" ሲሉ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ አስተያየታቸውን የሰጡ  የህግና የፖለቲካ ምሁራን ገለፁ።  ወይዘሪት ብርቱካን በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የሰሩ በመሆናቸው  የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ይወጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ምሁራኑ ተናግረዋል ። በዩኒቨርሲቲው የህግ ኮሌጅ ዲን አቶ ሆነልኝ ኃይሌ በሰጡት አስተያየት "ከዚህ በፊት በተካሄዱ ምርጫዎች ገለልተኛ አለመሆን የተስተዋለባቸውና ታማኝነት የጎደላቸው ነበሩ" ብለዋል ። ምክር ቤቱ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መምረጡ ቀጣይ የሚካሄደውን ምርጫ ታማኝና ፍትሃዊ እንዲሆን ከማስቻሉም ባለፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እኩል ያሳተፈ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል ። ወይዘሪት ብርቱካን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የሰሩ መሆናቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ አንድ ማሳያ ነው" ሲሉ አቶ ሆነልኝ ተናግረዋል ። በዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ሀብቴ አዳነ በበኩላቸው "ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸው  በህዝብና በፖለቲከኞች ዘንድ መተማመንን ይፈጥራል " ብለዋል ። "ቀጣዩ ምርጫ ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል በማሳተፍ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ታማኝ እንዲሆን ወይዘሪቷ እንደሚሰሩ እጠብቃለሁ " ብለዋል ። ወይዘሪት ብርቱካን በህግና በፖለቲካ ያላቸውን ብቃት በመጠቀም ለህዝብ ተጠቃሚነትና ለፍትህ መስፈን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን ጨምረው  ገልጸዋል ። መንግስት መጭው ምርጫ ነጻና ተአማኒ እንዲሆን የያዘው እቅድ እንዲሳካ ሌሎች የምርጫ ቦርድ አስፈጣሚ አባላትን በጥናት መሰየም እንደሚገባው አቶ ሀብቴ ጠቁመዋል ። በደብረብርሃን ከተማ በፌደራልና ክልል ፍርድ ቤቶች የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ፍስሃ አባቡ "በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ምርጫ ቦርዱ አቅምና አቋም ያለው ሰው ያስፈለገዋል" ብለዋል፡፡ "የወይዘሪት ብረቱካን የምርጫ ቦርደ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው ከዚህ ቀደም በድምፅ ቆጠራና በሌሎች የምርጫ ሂደቶች ህዝቡ ምርጫ ተጭበርበሯል በሚል የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለማስቀረት አስተዋጻ አለው" ብለዋል ። እንደ አቶ ፍሰሀ ገለጻ ምክር ቤቱም ሆነ መንግስት ወይዘሪት ብርቱካንን በመምረጥ ያሳዩት ቁርጠኝነት ተገቢ ነው። "ወይዘሮ ብርቱካንም እውቀታቸውን ተጠቅመው መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ ሊወጡ ይገባል" ሲሉ አቶ ፍስሃ አስታውቀዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መሾሙ ይታወቃል ።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም