የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

139
አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ። ከአሥራ አንዱ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የሆነው የቤተ ጎልጎታ-ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላለፉት 11 ወራት ሲካሔድለት የነበረው ጥገና ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል። በምረቃው ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት ቅርሶቹን ለመታደግ መንግሥት፣ አጋር ድርጅቶችና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም በቤተ ጎልጎታ - ሚካኤል ቤተክርስቲያን በተከናወነው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች ለሌሎች ተግባራት መፍትሔ የምንሰጥበት ሁኔታ ፈጥሮልናል ብለዋል። ተተኪ የሌለውን ጥንታዊ ቅርስ የመጠገን ኃላፊነት አምኖ የሰጣቸውን የላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ ያመሰገኑት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር በበኩላቸው ኤምባሲው በኢትዮጵያ የሚሠራቸው የጥገና ሥራዎች ኢትዮጵያውያንን በማሰልጠን የሚካሔድ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራው ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ውጤታማ የቅርስ ጥናት ፕሮጀክቶችን መሠረት በማድረግ የቀሪ ዐቢያተ ክርስቲያናትን ጥገና በፍጥነት ማካሔድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፤ ቤተክርስቲያኗ ለቅርሱ የጥገና ሥራ 20 ሚሊዮን ብር መመደቧን አስታውሰው ወደፊት ለሚካሔዱት የመፍትሔ ተግባራትም ከመንግሥት ጋር በመሆን ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ተናግረዋል፡፡ ቅርሱን መታደግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ የቤተ ጎልጎታ - ሚካኤል ቤተክርስቲያን የጥገና ሥራ የተከናወነው ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ በተገኘ 580 ሺህ እንዲሁም ከዓለም ቅርስ ፈንድ በተገኘ የ150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ነው። ከስምንቱ የዓለም እጅግ ድንቅ ሥፍራዎች አንዱ የሆነው የላሊበላ ውቅር ዐቢያተ ክርስቲያናት መካከል የቤተ ገብርኤል - ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ጥገናው መከናወኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም