የመጀመሪያው አዲስ የፊልምና የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ከነገ በስቲያ ይጀመራል

149
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010  የመጀመሪያው አፍሮ አቲያቲክ ኢንተርቴይመንት፣ አፍሮ ሴንቸሪ ኢቨንትስና ብሪቲሽ ካውንስል በጋራ ያዘጋጁት አዲስ የፊልምና የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በቫምዳስ ሲኒማ ይካሄዳል። የአፍሮ አቲያቲክ ኢንተርቴይመንት ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ይብራህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ደረጃ ፊልምና ፎቶ ያጣመረ አውደ ርዕይ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የፊልምና የፎቶ ባለሙያዎች የርስ በርስ ትውውቅ እንዲያደርጉና ልምምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ የአውደ ርዕዩ ዋንኛ አላማ እንደሆነ ገልጸዋል። አውደ ርዕዩ በፊልምና ፎቶ ኢንዱስትሪ ያሉ ባለሙያዎች ያላቸውን ክህሎት ለማዳበርና አቅማቸውን ለማጎልበት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። በፊልምና ፎቶ ዙሪያ የተሰሩ አጫጭር ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡ ገልጸው በአፍሪካ ደረጃ ስማቸው ከሚጠሩ የፎቶግራፍ ባለሙያ አንዱ የሆነው አሮን ስሜነህ በአውደ ርዕዩ ለተሳታፊዎች ተሞክሮውን እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል። በአውደ ርዕዩ ሁለተኛ ቀን በአነስተኛ በጀት ውጤታማ የሆኑ የፊልምና የፎቶ ፕሮጀክቶችን መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድ አቶ ብሩክ አስረድተዋል። በተጨማሪም "ፕሌይንግ ዊዝ ዘ ካሜራ" በሚል የፊልምና የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ያልሆኑ ተሳታፊዎች በቫምዳስ ሲኒማ ውስጥ ፊልም እንደሚቀርጹና ፎቶ እንደሚያነሱ ተጠቁሟል። በአዲስ አበባም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የፊልምና የፎቶ አወደ ርዕይ የማዘጋጀት ልምድ እንደሌለ የገለጹት አቶ ብሩክ በዚህ ረገድ ያለውን ልምድ ለመቀየር የአዲስ የፊልምና የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በር ይከፍታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። በቀጣይ የፊልምና የፎቶ ግራፍ አውድ ርዕይን ስፋት ባለው መልኩና በየጊዜው ለማካሄድ ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል። በአጠቃላይ በሁለት ቀኑ አውደ ርዕይ እስከ 500 ተሳታፊዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም