በምስራቅ ጎጃም ዞን በኩታገጠም የለማ የስንዴ ሰብል በኮምባይነር እየተሰበሰበ ነው

66
ደብረ ማርቆስ ህዳር 12/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን በ140 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በኩታገጠም የለማ የስንዴ ሰብል በኮምባይነር የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንዳስታወቁት በኩታገጠም የለማውን የስንዴ ሰብል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ  የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመሰብሰብ ሥራ እየተሰራ ነው። በመኽሩ የለማውን የስንዴ ሰብል በ60 ኮምባይነሮች ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በእዚህ ሳምንት ብቻ 14 ኮምባይነሮች ወደ አካባቢው ተጉዘው የደረሰ ሰብል የመሰብሰብ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። ፈጥነው ወደ ሥራ በገቡት ኮምባይነሮችም በ163 ሄክታር ላይ የነበረ የስንዴ ማሳ መሰብሰብ እንደተቻለ ገልጸው፣ በእዚህም ከ7 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት በዝናብ ሳይጎዳ ለመሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል። ወደሥራ የገቡትን ኮምባይነሮች በመጠቀም 500 አርሶ አደሮች ሰብላቸውን እንደሰበሰቡ የገለጹት አቶ አበባው ኮምባይነሮቹ በዩኒዬኖች፣ በግል ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች በኮንትራት የመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ስንዴና ሌሎች የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል በተማሪዎች እገዛ ጭምር በግልና በቡድን በተከናወነ የሰብል ስብሰባ ሥራም ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የነበረ ምርት መሰብሰቡን አቶ አባበው አስረድተዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ የጓይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አንዳርጌ አውለው በበኩላቸው በአንድ ሄክታር ላይ ያለሙትን የስንዴ ሰብል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል። ምርቱ በሰው ጉልበት ቢሰበሰብ ኑሮ ከ15 ቀን በላይ ይወስድባቸው እንደነበር የገለጹት አርሶ አደሩ ቀደም ባሉት ጊዜያት በባህላዊ መንገድ ሲሰበሰብ በዝናብና በንፋስ ምርታቸው ይጎዳ እንደነበር አስታውሰዋል። " በአሁኑ ወቅት ኮምባይነር በመጠቀሜ 3 ስዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምርቱን ከገለባው በመለየት ወደቤት ማስገባት ችያለሁ" ብለዋል። በኮንትራት ለመጣው ኮምባይነር በአንድ ኩንታል 80 ብር የኪራይ ዋጋ መክፈላቸውንም ጠቁመዋል። በባሶሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈንታሁን ያዜ በበኩላቸው እንዳሉት በኩታገጠም የዘሩትን አንድ ሄክታር የስንዴ ሰብል ትናንት በኮምባይነር ሰብስበው ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት። ምርታቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሰብሰባቸው ጊዜ እና ጉልበት ከመቆጠባቸው በተጨማሪ ምርቱን ከብክነት የታደገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ያለሙትን ሰብል በሰው ጉልበት ቢሰበስቡም ከማሳው ላይ ቶሎ ባለመነሳቱ በእንስሳት፣ በአዕዋፍትና በነፋስ ባክኖ ከ4 ኩንታል በላይ ምርት እንደቀነሰባቸው አስረድተዋል። " ዘንድሮ ካለፈው ዓመት ትምህርት በመውሰድ የኮምባይነር ተጠቃሚ ለመሆን በመመዝገብ ከ3 እስከ 4 ስዓት ባለ ጊዜ ውስጥ 45 ኩንታል የግብርና ምርት መረከብ ችያለሁ " ብለዋል። በዞኑ በመኽር ከለማው 650 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም