ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በጎዳናዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፖርቶችን መሰጠት ሊጀመር ነው

167
አዲስ አበባ ህዳር 12/2011 በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የግንዛቤ ማስጨበጫው የትራፊክ መንገዶችን ነጻ በማድረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እንደሚከናወንም ተጠቅሷል።። በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚሞተው ሰው 52 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን አማካሪ የሆኑት ዶክተር ውባዬ ዋለልኝ ጤናማ  ባልሆነ አመጋገብ፣ በቂ እንቅስቃሴ ካለማድርግ፣ ሲጋራ ከማጨስ፣ አልኮል አብዝቶ ከመጠቀምና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዘው ሰው ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። ይህን ለመከላከል ደግሞ በወሩ መጨረሻ እሁድ ቀን መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ የጤናና አካል ብቃት ስፖርቶች የሚከናወኑ ይሆናል። እንዲሁም ነጻ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊትና  ሌሎች ህመሞች ምርምራ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችም ይኖራሉ ተብሏል። ይህ ስራ ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሚጀመር ሲሆን ምርምራውም ሆነ ስፖርታዊ  እንቅስቃሴዎች የሚሰጡት በነጻ ነው ተብሏል። ይህ ስራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ በሌሎች የክልል ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የተነገረው። ይህን ስራ በተቀላጠፈ መልኩ ለመስራትም ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ በባህል ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ መሪዎች ጋር የጋራ የምክከር ስራዎች እየተደረጉ መሆኑም ተጠቁሟል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም