በኢጋድ የቀረበው የሰላም ሀሳብ የደቡብ ሱዳናዊያንን ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

50
አዲስ አበባ  ግንቦት 16/2010 የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን/ኢጋድ/ አማካኝነት የቀረበው አዲሱ የሰላም ሀሳብ በአገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሲሉ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱም ጥሪ ቀርቧል። ላለፉት ስድስት ቀናት በአዲስ አበባ በተለያዩ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሲካሄድ የነበረው ስብሰባ ተጠናቋል። በዚሁ ወቅት የኢጋድ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት ንግግር ኢጋድ ለተሰብሳቢዎቹ  ያቀረበው የሰላም ሀሳብ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን አስፈላጊ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለሰላም ሀሳብ ሂደቱ ድጋፍ ላደረጉት  ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአውሮፓ ህብረት፣ ለቻይና፣ ለጃፓን እንዲሁም አሜሪካ፣ ኖርዌይና እንግሊዝ አባል ለሆኑበት ትሮይካ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የደቡብ ሱዳን አብያተ-ክርስቲያናት ምክር ቤት የሴቶችና የወጣቶች ቡድኖች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ አባላት በፓርቲዎቹ መካከል ውይይት እንዲደረግ ያደረጉትን ጥረትም ዶክተር ወርቅነህ አድንቀዋል። በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢስማኤል ዋይስ በበኩላቸው ውይይቱ በተካሄደባቸው ቀናት የሰላም ሂደቱን በማመቻቸት የአገሪቱ አብያተ-ክርስቲያናት ምክር ቤት ላበረከቱት አስተዋዕኦ አመስግነዋል። በደቡብ ሱዳን የጋራ ክትትልና ግምገማ ኮሚሽን ረዳት ተጠሪ አምባሳደር ብርሀኑ ከበደ የድርጅቱን ሊቀ-መንበር ወክለው ባደረጉት ንግግር ኢጋድ ያቀረበው የሰላም ሃሳብ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም ፓርቲዎቹ ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ሲሉ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል። በቅርቡ የኢጋድ ሚኒስትሮች ካውንስል ስብሰባ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም