በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት አቶ ያሬድ ዘሪሁን ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል

70
አዲስ አበባ ህዳር 12/2011 በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞው ምክትል ኃላፊ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ያሬድ ዘሪሁን ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ያሬድ ባለሙያ አማክረው ለዛሬ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል። በዚሁ መሰረት በዛሬው የችሎት ውሎ ሁለት ጠበቃ አቁመው ቀርበዋል። ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ ጋር በመመሳጠርና በጥቅም በመተሳሰር ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተቀብለው በርካታ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀማቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። አቶ ያሬድ በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ስውር እስር ቤት እንዲገቡ፣ በጨለማ እንዲቆዩ፣ ብልታቸው በፒንሳ እንዲሳብ፣ ብልት ላይ ውሃ የያዘ ፕላስቲክ ማንጠልጠል፣ እርቃናቸውን ጉንዳን ማስበላት፣ ጫካ ውስጥ ብቻቸውን እንዲሆኑና ሌሎች ኢ – ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀምባቸው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። ይህም ተግባር ህግ የማይፈቀደውና ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር እንደሆነ አስረድቷል። ወንጀሉ ውስብስብና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለምርምራው የሚያስፈለግና የተጎጂዎችን የህክምና ጉዳይ መርምሮ ውጤት የማቅረብ ስራ ስለሚጠይቅ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፖሊስ ጠይቋል። የተጠርጣሪ ጠበቆች በአቶ ያሬድ የእስር ቤት አያያዝና የቤተሰብ ጥየቃ ላይ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ አንጻራዊ መሻሻል እንደታየና በዚህም ምክንያት አቤቱታቸውን ማንሳታቸውን ያም ቢሆን የተጠርጣሪ ጠበቃ በእስር ቤት ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኛት እየቻሉ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ፖሊስ እስካሁን በተጠርጣሪው ተፈጸሙ ካላቸው ወንጀሎች ጋር የሚያገናኛቸውን በቂ ማስረጃ እንዳላቀረበና የሚቀርበው ጉዳይም ድግግሞሽ እንደሆኑ ጠበቆቹ ገልጸዋል። ህጉ በሚያዘው መሰረት መርማሪ ፖሊስ ከተጥርጣሪው ቃል መቀበል ሲገባው እስካሁን ቃል እንዳልተቀበለ አመልክተዋል። ካሉበት ሁኔታ የጤና ሁኔታ አንጻርና የለውጡ አካል እንደመሆናቸው መጠን በዋስ ቢለቀቁ የወንጀል ምርምራው ላይ ምንም አይነት መሰናክል እንደማይፈጥሩ ገልጸዋል። ጠበቆቹ ከአቶ ያሬድ ጋር በነበራቸው ውይይት አሁን በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የለውጥ ሂደት የሚደግፉና እየተካሄደ ያለውም ለውጥ አገሪቷን እንደሚጠቅማት እንደሚያምኑ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል። ተጠርጣሪ አቶ ያሬድ በሚዲያና በመንግስት በኩል የሚታዩ የተሳሳቱ አገላለጾች በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደሩ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ''በሚሰራጩ መረጃዎች ላይ ላለፉት 27 ዓመታት በነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ተሳትፎ አለው'' በሚል የሚገለጸው አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል። ''እኔ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞው ምክትል ኃላፊ ሆኜ የሰራሁት ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ነው ተቋሙ ውስጥ የተሾምኩት የብሔር ተዋጽኦ በሚል ነው'' ሲሉ በተቋሙ የነበራቸውን የቆይታ ጊዜ ገልጸዋል። ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ዓመት በደቡብ ክልል የደህንነት አስተባባሪ እንደነበሩና በስራቸውም ምስጋና እንደተቸራቸውና ይህንንም ጉዳይ ከህብረተሰቡ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል። ''የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ቀጥታ ትዕዛዝ መስጠት የሚችለው ዋና ዳይሬክተሩ ነው የኔ ተግባር መረጃዎችን ወደ ላይ ማስተላለፍና ከላይ የሚመጡ መረጃዎችን ወደ ታች ማውረድ ነው በሚባሉት ነገሮች ላይ እኔ ምንም ተሳትፎ የለኝም'' ብለዋል። ''ተቋም ውስጥ በተቀጠርኩበት ጊዜ በተደጋጋሚ ባለኝ ተቃርኖና ባለብኝ አምስት ጊዜ ኦፕራሲዮን ተደርጌ ህመሜ የከፋ በመሆኑ ስራ ለመልቀቅ ለአቶ ጌታቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ደብዳቤ ባቀረብም ትንሽ ታገስ'' በማለት እንዳቆዩዋቸው ገልጸዋል። ስራውንም ከለቀቁ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠው የተወሰነ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ ባለባቸው ህምም ስራውን መቀጠል እንደማይችሉ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት እንዳገኙ ጠቅሰዋል። ከዶክተር አብይ ጋር የቅርብ ትስስር እንዳለቸውና ባላቸው የስራ ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ቀርቦላቸው ''ቀጣይ አገሪቷን ማገልገል በምትችለበት ቦታ እሾማለሁ ብለውኝ ያንን ምደባ በምጠባበበቅበት ወቅት ነው ይህ ነገር የተፈጠረው'' ብለዋል። ካለኝ የህግ አክባሪነት አንጻር በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ስልክ ተደውሎልኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠርጥረሃል ልናናግርህ እንፈልጋለን ቢሉኝ ቀጥታ ቢሮዋቸው ድረስ ሄደው ቃላቸውን መስጠት እንደሚችሉና ያም ቢሆን የተያዙበት መንገድ ግን አግባብነት የሌለው እንደሆነ ገልጸዋል። ''እኔ ከመያዜ በፊት ቤቴ ተሰብሯል አራት ልጆቼ ታግተዋል ይሄንን ስሰማ ራሴን ላጠፋ ነበር ነገር ግን ለልጆቼና ለቤተሰቦቼ ስል ያንን ነገር ትቼዋለሁ'' ብለዋል። ሲያዙ በሚወጡ መረጃዎች የተንደላቀቀ ባለ ኮከብ ሆቴል ውስጥ ሆነው 'ሲፈለግ ተሰውሮ ነበር' የሚለው ጉዳይ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ተናግረዋል። የተያዙበት ቦታ ዱከም ምንም አይነት ባለ ኮከብ ሆቴል የሌለውና የነበሩበት ሆቴልም ዝቅተኛ ደረጃ ያለው እንደነበረም አውስተዋል። ዱከም የነበሩት ከባለቤታቸው ዘመዶች ጋር እንደሆነና ልክ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ናት ምንም አይነት ድንበርና ፓስፖርት አያስፈልገም የትም አልተደበቁም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በአጠቃላይ ባለው ሁኔታ ያለው ጉዳይ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው ብለዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠርጣሪ ቃል ያልተቀበለው ተጨማሪ መረጃ በመሰብሰብ መረጃ ለማደራጀት እንደሆነ ገልጿል። በተጨማሪም ከ60 በላይ የቃል ምስክሮችን እንደሚቀበልና ቃል ምስክር የምንቀበላቸው ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች ይገኛሉ ብለዋል። ተጠርጣሪው በዋስ ከወጡ መረጃዎች ያበላሹብናል በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ የዋስ ጥያቄው ውድቅ ሆኖ ተጨማሪው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። የተጠርጣሪ ጠበቆች ደንበኛቸው የተከሰሱበት ወንጀል በግልጽ እንዲነገራቸው በጠየቁት መሰረት ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ይዞ  ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ መርማሪዎች የምርመራ መዝገቡን መያዛችውን መርማሪዎቹን ሲጠይቁ መዝገቡን አለመያዛቸውን ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ያሬድ ዘሪሁን የተከሰሱበትን የምርመራ መዝገብ ፖሊስ ለነገ ከሰዓት በኋላ ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም