ውቅር ዐቢያተ ክርስቲያናቱን ለመታደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት አለባቸው

73
ህዳር 12/2011 የላሊበላ ውቅር ዐቢያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ መንግሥት፣ አጋር ድርጅቶችና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡ ከአሥራ አንዱ የላሊበላ ውቅር ዐቢያተ ክርስቲያናት የቤተ ጎልጎታ - ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላለፉት 11 ወራት ሲካሔድለት የነበረው ጥገና ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል። በምረቃው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት በቤተ ጎልጎታ - ሚካኤል ቤተክርስቲያን በተከናወነው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች ለሌሎች ተግባራት መፍትሔ የምንሰጥበት ሁኔታ ፈጥሮልናል ብለዋል። ተተኪ የሌለውን ጥንታዊ ቅርስ የመጠገን ኃላፊነት አምኖ የሰጣቸውን የላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ ያመሰገኑት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር በበኩላቸው ኤምባሲው በኢትዮጵያ የሚሠራቸው የጥገና ሥራዎች ኢትዮጵያውያንን በማሰልጠን የሚካሔድ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራው ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል። የቤተ ጎልጎታ - ሚካኤል ቤተክርስቲያን የጥገና ሥራ የተከናወነው ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ በተገኘ 580,000 ዶላር እንዲሁም ከዓለም ቅርስ ፈንድ በተገኘ የ150,000 የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ነው። ከስምንቱ የዓለም ድንቅ ሥፍራዎች አንዱ የሆነው የላሊበላ ውቅር ዐቢያተ ክርስቲያናት መካከል የቤተ ገብርኤል - ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ጥገናው መከናወኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም