ታዳሽ ኃይል ታዳሽ ሐብት

357

ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ)በርካታ የገጸ ምድር ሐብት ከታደሉ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ብዙ የአለም አገሮች ሞቃታማ፣ ሐሩራማ፣ ቀዝቃዛ እንዲሁም በረዶ የሞላው የአየር ፀባይ ሲላበሱ ኢትዮጵያ ግን ሁሉንም የአየር ጸባይ ያማከለ ነባራዊ ሁኔታ የሚታይባት ነች። ኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ የሚታይባቸውን ዘርፈ ብዙ የታሪክና የተፈጥሮ ሐብቶችን ለአለም ያበረከተች ቢሆንም በጀመረችው የጥበብ ጎዳና መራመዷን በመግታቷ  ቀደምት መባሏ ቀርቶ ኋላቀር ተብላ እየተጠራች ትገኛለች።።

የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ጸባይ ለእርሻና ለኃይል ማመንጫ ያለው ተስማሚነት የተመሰከረለት ቢሆንም ጥቅም ላይ መዋል የቻለው ግን ከእጅ ጣት ቁጥር የማያልፈው ብቻ ነው። በተለይ አገሪቱ ያላት እምቅ የታዳሽ ኃይል ሐብት ከራሷ አልፎ በድህነት አረንቋ ለሚዳክሩት ጎረቤቶቿ ተስፋን ያዘለ ነው። ነገር ግን ይህንን ሃብት ወደ ተግባር ለመቀየር የተጓዝንበት ርቀት አጭር ቢሆንም ተስፋዎች ግን መፈንጠቅ ጀምረዋል። በተለዋዋጩ የአለም የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ታዳሽ ኃይል ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባሻገር ፖለቲካዊ አንድምታውም የሚናቅ አይደለም፡፡ አሁን አሁን ታዳሽ ኃይል የአገሮችን የርስ በርስ ግንኙነት እስከመወሰን ደርሷል፡፡ ከታዳሽ ኃይል በሌላ ጽንፍ የቆመው የነዳጅ ሃይል ካለበት ውስንነት ወይም አላቂነት አኳያ ታዳሽ ሃይልን የመምረጥ ጉዳይ በርግጥም ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው፡፡ በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያረጋግጡት፤ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መርሃ ግብርን በአግባቡ በመተግበር ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን በግንባር ቀደምትነት እየተወጣች ነው። ታዳሽ ኃይል በኢትዮጵያ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የሚቀዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አራት ዋና ዋና መሰረታዊ ነጥቦችን እንደያዘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የመጀመሪያው የግብርና ልማትና የመሬት አጠቃቀም ብቃትን ማምጣት ነው፡፡ ሁለተኛው የደን ልማትና ጥበቃ ስራን ኢኮኖሚያዊና የስነ ምህዳር ስርዓትን በሚጠቅም አግባብ ያስኬዳል፡፡ ሶስተኛው ተገቢ የተሻሻሉና ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአንዱስትሪ ልማት፣ ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለግንባታ ስራዎች መጠቀምን ይይዛል፡፡ አራተኛው ታዳሽና ንጹህ ኃይልን የማመንጨት ልማት ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦችም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ከግብ ያደርሳሉ የሚባሉ ናቸው።አገሪቱ ካላት የታዳሽ ኃይል ሃብት ጥቅም ላይ እንዳልዋለ የሚታወቀው የእንፋሎት ኃይል በዘርፉ ከፍ ያለ ለውጥ የማስመዝገቢያው ቀጣይ መስመርም መሆን ይችላል። በተለይ የእንፋሎት ኃይልን በተመለከተ ከአዲስ አበባ በ270 ኪ.ሜ ርቀት፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻላ ወረዳ ከዞኑ መዲና ሻሸመኔ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኮርቢቲ ቀበሌ ዕምቅ የእንፋሎት ሀብት ከሚገኝባቸው የስምጥ ሸለቆ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ስፍራ በከርሱ አምቆ የያዘው እሳተ ጎመራ የሚፈጥረው እንፋሎት እስከ 10 ሺህ ሜጋ ዋት የሚደርስ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ የጂኦተርማል ሀብት እንዳለው የኢትዮጵያ ጂኦሎጆካል ሰርቬይ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ መናገራቸውን ቲንክ ጂኦ-ኢነርጂ የተባለ ድረ ገጽ በመጋቢት 2018 (እአአ) እትሙ አስፍሮታል። ይህን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው 150 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ከዳሎል እስከ ኬንያ ድንበር ባለው የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ለጂኦተርማል ኃይል መዋል የሚችሉ ከ22 በላይ አካባቢዎች ተለይተዋል። ኢትዮጵያ ያላትን የጂኦተርማል እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥታ በመረባረብ ላይ ከምትገኝባቸው አካባቢዎችና ዘርፎች መካከልም የኮርቢቲ ቀበሌ አንደኛው ነው፡፡ ከወንዞች ኃይል ለማመንጨት እየተከናወነ ካለው ተግባር ጎን ለጎን ለጂኦተርማል ኃይል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተንዳሆ 100፣ ኮርቤቲ 75፣ አባያ 100፣ ቱሉ ሞዬ 40 ሜጋ ዋትና ዶፋን ፈንታሌ 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው። ከሶስት አመት በፊት ይፋ የተደረገው የኮርቤቲና ቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ስራ የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል ሲሆን፤ 1000 ሜጋ ዋት /በኮርቤቲ 500 በቱሉ ሞዬ 500/ ኃይል ለማመንጨት ለእያንዳንዱ 2 ቢሊዮን በአጠቃላይ 4 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦ ስምምነቱን የተፈራረመው ሬይኪያቪክ ጂኦተርማል የተሰኘ የአይስላንድ ኩባንያ ወደ ስራ ገብቷል ፡፡ በአሁኑ ወቅት 500 ሜጋ ዋት የሚሆነውን የጂኦተርማል ኃይል ለማመንጨት የሚያስችለውን ስራ ለመጀመር በርክሌይ ኢነርጂና አይስላንድ ድሪሊንግ የተሰኙ ሁለት ኩባንያዎች በኮርቤቲ የመንገድ የውሀና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወኑ ስለመሆናቸውም በድረ ገጹ ላይ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ የበርካታ ወንዞች ባለቤት በመሆኗ የተለያዩ ግድቦችን በመገደብ ለሀይል ማመንጫነት እያዋለች ቢሆንም፤ የአየር ንብረት ለውጥ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የወንዞች የውሃ መጠን ሊቀንስ ብሎም ሊደርቅ ይችላል። በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ሊደርስበት የማይችለውን የጂኦተርማል ሀብት መጠቀም የግድ መሆኑን በማስላት አገሪቱ የንፋስ፤ የጸሀይና የጂኦተርማል አማራጮችን ለመጠቀም እየሰራች መሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ነው፡፡ አማራጩን መጠቀም የሚያስፈልገው ደግሞ  ከአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን፤ ከጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት ስራ ውስብስብ ያልሆነና ቀላል ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችል መሆኑ ነው። በተጨማሪ አቅሙን በቀላሉ እያሳደጉ መቀጠል የሚያስችል ዘርፍ ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በአፍሪካ ለጂኦተርማል የሀይል ምንጭ መዋል ከሚችለው የተፈጥሮ ሃብት 60 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮያ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የኮሙኒኬሸን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዢንዋ እንደተናገሩት፤ አገሪቱ ከ 2017 እስከ 2025 (እኤአ)  ለስምንት አመት የሚዘልቅ የኤሌክትሪክ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ እየተንቀሳቀሰች ነው። በዚህም አሁን በአገሪቱ ያለውን 58 ነጥብ 13 በመቶ የኤሌትሪክ ሽፋን እኤአ በ2025 ወደ መቶ በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው  ጠቅሰዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአለም አቀፉ የኤሌትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈገልገው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 375 ሚሊዮን ዶላር ከአለም ባንክ በብድር ማግኘት መቻሉንም አቶ ብዙነህ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ አሁን ያለውን 4 ሺህ 280 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል እኤአ በ 2025 ወደ 17 ሺ 300 ሜጋ ዋት በማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። በኢትዮጵያ የሀይል አጠቃቀም ዙሪያ ከአመታት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የውሃ ኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ አንድ በመቶ፤ ከነዳጅ ከሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል 4 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የኃይል ምንጭ የሚገኘው ከደን፤ ከእንስሳትና ከሰብል ተረፈ ምርት ነው፡፡ አብዛኛው ነዳጅ ለተሽከርካሪ ጥቅም ይውላል፡፡ በዓመት 40 ሚሊዮን ቶን ማገዶ እንጨትና 8 ሚሊዮን ቶን የሰብል ተረፈ ምርት በኃይል ምንጭነት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ስለሆነም በተፈጥሮ ሀብት መመናመን የተነሳ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ከውሃ ከሚገኘው ታዳሽ ኃይል ጎን ለጎን የጂኦተርማል ሃይል ልማት ላይ ማተኮር የግድና ለነገ የማይባል ስራ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም