ለ20 ዓመታት ያለልማት ታጥሮ የነበረው ቦታ ወደ መሬት ባንክ ተመለሰ

207
አዲስ አበባ ህዳር 12/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሚድሮክ ኢትዮጵያ በፒያሳ አካበቢ ለልማት ብሎ አጥሮ ይዞት የነበረውን ከ33ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት አጥር የማፍረስና ንብረት የማንሳት ስራ በማከናወን መሬቱን በዛሬው እለት ወደ መሬት ባንክ የመመለስ እርምጃ ወሰደ። የሚድሮክ ኢትዮጵያ በበኩሉ እርምጃው የአገሪቷን ህግ ያልተከተለ ነው ብሎታል። የከተማዋ መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ተስፋዬ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ለልማት ተብለው በተለያዩ ወገኖች ታጥረው የነበሩ ቦታዎች አጥር የማፍረስና ንብረት የማንሳት ስራ በሁሉም ፕሮጀክቶች ላይ እየተሰራ ነው። በዛሬው እለትም ከ20 ዓመት በላይ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን በፒያሳ አካባቢ ሳያለማው የቆየውን መሬት ወደ መሬት ባንክ የማስመለስ ስራ ተሰርቷል ሲሉ ተናግረዋል። ውሳኔው ከተላለፈበት ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ፣ አልሚዎቹ እንዲያውቁትና ንብረታቸውን እንዲያነሱ የማሳወቅና በተጨማሪም በክፍለ ከተማዎች በኩል ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ርምጃው መወሰዱን ገልጸዋል። የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ባሲም አል-ዳሂር በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እየወሰደ ያለው እርምጃ አገሪቷ ያወጣችሁን ህግ ያልተከተለና ሙሉ በሙሉ ህግን በጣሰ መልኩ የተከናወነ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የአገሪቷ ህግ መሬት ከአልሚዎች ወይም ከመሬት ባለቤቶች ለመውሰድ በትንሹ የሶስት ወር ጊዜ እንደሚሰጥ የሚፈቅድ ሆኖ ሳለ የሰባት ቀን ጊዜ ብቻ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ''ይህም ንብረቶቻችንን በአግባቡ እንዳናነሳና እንዳንወድስ አድርጎናል'' ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው ደግሞ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ለ20 ዓመታት ያላለማው መሬት ላይ ጊዜ ስጡኝ ማለቱ የመንግስትና የህዝብ ሃብትን ለብክነት የበለጠ የሚዳርግ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት መሬቱን ለማልማት ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ለልማት የሚሆኑ የኮንስትራክሽ እቃዎች በቦታው ላይ አለመኖራቸውን ገልጸዋል። ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ውስን የሆነው የመንግስትና የህዝብ ንብረት እንዲባክን መፍቀድ መሆኑ ታውቆ እርምጃው ህግን ተከትሎ እንዲወሰድ መደረጉን አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት ተቋማት፣ በዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና በግለሰቦች ለአመታት ሳይለሙ የቆዩ 154 ቦታዎችን ወደመሬት ባንክ እንዲገቡ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም