የፋይናንስ ዘርፉ በግንባታ ኢንዱስትሪ ላይ ስላለው ሚና ያተኮረ ስብስባ ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

59
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 የፋይናንስ ዘርፉ በግንባታ ኢንዱስትሪው ላይ ስላለው ሚና የሚመክር ስብስባ ከነገ በስቲያ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ሲቪል መሐንዲሶች ማህበር ያዘጋጀው ስብስባ "ባንኮችና ኢንሹራስ ኩባንያዎች ለዘላቂ የግንባታ ኢንዱስትሪ እድገት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ተስፋዬ ወርቅነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፋይናንስ ዘርፉ በግንባታ ኢንዱስትሪ እየተወጣ ያለውን ሚና መዳሰስ የስብሰባው ዋንኛ አላማ ነው። ብዙ በጀት እየፈሰሰበት የሚገኘው የግንባታው ኢንዱስትሪ ውስጥ የፋይናስ ተቋማት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦና ከግንባታ ኢንዱስትሪው ጋር ያላቸው ትስስር ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል። በግንባታው ዘርፍ ያሉ መሐዲሶች የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ሌላው የስብስባው አላማ እንደሆነ ተናግረዋል። በስብሰባው ላይ መሪ ሀሳቡን የተመለከቱ ሁለት የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውና በውይይቱ ማጠናቀቂያ በተነሱት ጉዳዮች ላይ የመፍትሔና የትኩረት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል። በቀጣይም በግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮሩ አውደጥናቶችና ስብሰባዎች ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን አክለዋል። በውይይቱ ላይ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከመንግስትና የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ከግንባታው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ 300 ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ተገልጿል። የኢትዮጵያ መሐንዲሶች ማህበር የተመሰረተው ከ55 ዓመት በፊት ሲሆን 1ሺህ500 አባላት አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም