ዩኒቨርሲቲ - የመቀራረብና የአብሮነት መድረክ !

87
ምናሴ ያደሳ(ኢዜአ) የተለያየ ባህል ፣ ቋንቋና ማንነት በአንድ ሀገር ውስጥ መኖር  ከምንም በላይ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ የሰው ልጅን ከሌሎች ፍጡራን የሚለየው ባህል ፣ ቋንቋና ማንነቱ ነው ፡፡ ባህል ከሰው ልጅ ውጪ በሌሎች ፍጡራን ዘንድ አይገኝም ፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ በብዛት ሲኖር የዚያን ሀገር ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ የተለያዩ ባህል ፣ ቋንቋና ማንነት በአንድ ሀገር ውስጥ  መኖር ብቻውን የተሟላ ሀብት ወይም ውበት አይሆንም፡፡ እነዚህን ይዘው የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ላይ ተገናኝተው እርስ በእርስ ሲቀላቀሉ እና ሲተዋወቁ አንዱ የአንዱን ባህል ቋንቋና ማንነት ሲረዳ እና ሲያጎለብት ነው ለሀገሪቱ የተሟላ ውበትና ሀብት ሊሆን የሚችለው፡፡ ባህል፣ቋንቋና ማንነቶች በተፈጥሮ ወይም በደም ውርስ የምናገኛቸው አይደሉም፡፡ ይልቁንም በማህበራዊ ህይወት ውስጥ በምናገደርገው ልምምድ ከራሳችን ጋር የምናዋህዳቸው ናቸው፡፡ የሚፀነሱት ፣ የሚወለዱትና የሚያድጉትም በማህበራዊ ግንኙነት መስተጋብር ውስጥ ነው፡፡ የአንድ ህብረተሰብ ወይም ማህበረሰብ አባላት በእርስ በርስ ግንኙነት የሚጋሩት ቅርስ ነው፡፡ ይህ  የአንድ ማህበረሰብ ቅርስ ወይም ሀብት ከሌላኛው ማህበረሰብ ባህል ወይም ቅርስ ጋር ሲዋሀድ ደግሞ በቀለም ያሸበረቀ ልዩ ውበት ይሆናል፡፡ ለዛ ነው የተለያዩ ባህል ፣ቋንቋና ማንነቶች በአንድ ቦታ ሲገኙ ውበት ናቸው የሚባሉት፡፡ በሀገራችን የተለያዩ ባህል፣ቋንቋና ማንነቶች ያሏቸው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ወይም ብሄር ብሄረሰቦች ቢኖሩም አብዛኛዎቹ ከመልክአምድር አቀማመጥ የተነሳ ተራርቀው ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ አንዱ የአንዱን ባህል፣ቋንቋና ማንነት የመጋራት እድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ዜጎች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና አንዱ የአንዱን የአኗኗር ዜይቤ  እንዲጋራ በመደበኛነት የሚገናኙበት መድረክ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በሀገራችንም በየአመቱ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን  በዜጎች መካከል መተዋወቅና መቀራረብ እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽዎ እያበረከተ ነው ፡፡ሆኖም ግን ግንኙነቱ አመት ጠብቆ መሆኑ በሚፈለገው ደረጃ መተዋወቅ የሚፈጥር አይሆንም፡፡ ከዚህም በላይ ለመተዋወቅ ለመቀራረብና እርስ በእርስ ለመጎዳኘት  የትምህርት ተቋማት  ትልቅ አስተዋጽዎ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የተለያየ ባህል፣ቋንቋና ማንነት ያላቸው ተማሪዎች የሚገናኙበትና ለረጅም ጊዜ አብረው የሚቆዩበት  ቦታ በመሆናቸው  ተመራጭ ናቸው፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን አዳዲስ ተማሪዎቹን ሲቀበል በቦታው ተገኝቼ ነበር፡፡ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በቂ እውቀት ቀስመው ከመውጣት ባለፈ ለእርስ በእርስ ግንኙነትና መተዋወቅ ምን ያህል ትኩረት ይሰጣሉ ጠቀሜታውንስ እንዴት ይገነዘቡታል  የሚለውን ለማወቅ ጥያቄዎች አቅርቤላቸው ነበር፡፡ ተማሪዎቹም የሚከተሉትን ምላሾች ሰጥተውኛል፡፡ የተማሪዎቹን ስሜት ተረድቼ የጠየኳቸው በሚመስል መልኩ ሁሉም በሰጡኝ ምላሽ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ለመቀራረብና አንዱ የአንዱን እሴቶች ለማወቅ እቅድ እንዳላቸው ነው የነገሩኝ፡፡ በመጀመርያ አስተያየቷን የሰጠችኝ ከአማራ ክልል ወረታ ከተማ የመጣቸው ተማሪ አማረች አንዱአለም ናት፡፡ እሷ እንዳለችው አስቀድማ የመቱ ዩኒቨርስቲን የመረጠችበት ምክንያት ከምትኖርበት አካባቢ ርቀት ላይ ስለሚገኝ ሀገሯን ለማወቅ ካላት ጉጉት በመነሳት ነው፡፡ “በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር በመተዋወቅና በመግባባት ጥሩ ግዜ አሳልፋለው የሚል እምነት አለኝ” ያለችው ተማሪዋ ይህም ጥሩ ውጤት እንድታስመዘግብና ደስተኛ እንደሚያደርጋት ተናግራለች፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፍቅር፣አንድነትና መደመር እየተሰበከ ባለበት ወቅት ዩኒቨርስቲ መግባቷ እድለኛ እንደሚያደርጋትም ገልጻለች፡፡  የአካባቢው ማህበረሰብ ነባር ተማሪዎችና የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ያደረገላት የፍቅር አቀባበል ይበልጥ ደስታ እንዲሰማት እንዳደረገም ትገልጻለች፡፡ ከቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ የመጣው ተማሪ ያዕቆብ ፈቃዱ በበኩሉ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ትምህርቱን በሚገባ ተከታትሎ ከመውጣት በተጨማሪ አንድ ለየት ያለ ዕቅድ ይዞ እንደመጣ ይናገራል፡፡ ከሌላ አካባቢ ከመጡ ተማሪዎች ጋር ይበልጥ መቀራረብና አንድነት በመፍጠር አንድ ሌላ ቋንቋ ይዞ  የመውጣት አላማ እንዳለው ነው የተናገረው፡፡ ባለፉት አመታት በሀገሪቱ በነበረው ችግር ዩኒቨርስቲዎች አካባቢ ሲታይ የነበረው የሰላም መደፍረስ የተነሳ ተማሪዎች ግዜያቸውን በአግባቡ ያለመጠቀማቸው እንደሚያሳዝነው ነው የገለጸው፡፡ ተማሪዎች የትምህርት ግዜያቸውን በአግባቡ ካለመጠቀማቸውም በላይ በብሄር ተለያይተው  ግጭት ውስጥ መግባታቸው ትልቅ  ስጋት ፈጥሮ እንደነበረም ተናግሯል፡፡ “ባለፉት አመታት የተፈጠሩ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ እና ዩኒቨርስቲ የሰላምና የፍቅር ቦታ እንዲሆን የሚጠበቅብኝን ሀላፊነት እወጣለው” ብሏል፡፡ ዩኒቨርስቲ የወደፊት ህይወት መሰረት የሚጣልበት ቦታ በመሆኑ  የፍቅር፣አንድነት እና መቻቻልን ባህል በማጎልበት ብቁ ዜጋ ሆኖ ለመውጣት እንዳለመም ነው ያብራራው፡፡ ባለፈው ክረምት በነበረው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች የሚኖሩበትን ዞን እና ክልል ተሻግረው በበጎ ፈቃድ ተግባራት እንዲሳተፉ መደረጉ ትልቅ ትምህርት እንደሰጠው ነው የገለጸው፡፡ ይህ እርስ በእርስ መቀራረብና መተዋወቅ ባህል እንዲጎለብትም በዩኒቨርስቲ ተግባራዊ በማድረግ አርአያ መሆን እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡ ተማሪ ኡቻር ኡጁሉ ከጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን በዩኒቨርስቲው የተመደበች አዲስ ተማሪ ናት፡፡በሰጠችው አስተያየትም በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ያለው አንድነትና መግባባት በዩኒቨርስቲ ግቢም ይተገበራል የሚል እምነት አላት፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች በዩኒቨርስቲ የሚገናኙ ተማሪዎች  በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ የተፈጠረውን መግባባት በማጎልበት አርአያ መሆን እንዳለባቸውም መክራለች፡፡ “ከትውልድ አካባቢዬ ወጥቼ ከሌሎች አካባቢ ተወላጆች ጋር ስገናኝ ለመጀመርያ ግዜ ነው” ያለችው ተማሪ ኡቻር በቆይታዋ የተለያዩ ባህል፣ቋንቋና ማንነት ይዘው ከሚመጡ ተማሪዎች በመቀራረብ ስለ ሀገሯ ለማወቅ እድል እንደሚፈጥርላትም ገልጻለች፡፡ “ሰላም ከሌለ ምንም ነገር አይኖርም” ያለችው ተማሪዋ ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የሚጠበቅባትን ሁሉ እንደምትወጣ ተናግራለች፡፡ በዩኒቨርስቲው የሁለተኛ አመት አካውንቲንግ ተማሪ ሀብቴ በፈቃዱ እንዳለው  በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከመቼውም ግዜ በበለጠ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከዩኒቨርስቲው አመራር ጋር ተቀናጅተን ለመስራት ተስማምተናል ብሏል፡፡ “ባለፈው አመት በግቢያችን ውስጥ በነበረው ያለመረጋጋት በትምህርት ግዜያችን ትልቅ ኪሳራ ደርሶብን ነበር” ብሏል፡፡ ያለፈው ችግር ዳግም እንዳይከሰት ከየዲፓርትመንቱ ካሉ ተማሪዎች ጋር በተማሪዎች ህብረት በኩል ተወያይተው  በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡ ባለፉት አመታት በዩኒቨርስቲው ውስጥ የነበረው ያለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ በዋናነት ከሀገራዊ የፖለቲካ ጥያቄ ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡” ያለው ተማሪው  አሁን ግን ችግሮች በተገቢው መንገድ እየተፈቱ በመምጣታቸው  ትኩረታቸውን ለትምህርት ብቻ በመስጠት በቂ እውቀት  ቀስመው ለመውጣት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጸው፡፡ አዳዲስ በዩኒቨርስቲው የተመደቡ ተማሪዎችም ከዚህ ቀደም የነበረው ችግር ይከሰታል ብለው እንዳይሰጉና ያለጭንቀት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ  በተማሪዎች ህብረት አማካይነት ከየዲፓርትመንቱ ከተመረጡ ሌሎች  ተማሪዎች ጋር ምክር እየሰጡ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በተማሪዎቹ የአቀባበል ስነስርአት ላይ የተገኙት በሰግለን ኢሉ የመቱ አባገዳ ተሰማ ሙሉነህ ተማሪዎቹ እርስ በእርስ ያላቸውን ፍቅር በማጎልበት በመረዳዳትና በመደጋገፍ በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን የመግባባት መንፈስ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ሊያጎለብቱ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ በትምህርት ህይወት የምትባክን እያንዳንዷ ደቂቃ ኋላ ላይ ለቁጭት የምትዳርግ በመሆኗ ተማሪዎቹ የወጣትነት ስሜታቸውን በመግዛት የወደፊት ህይወታቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ሊጥሉ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ “እናንተ ተማሪዎች ለመጀመርያ ግዜ ከቤተሰቦቻቹ ተለይታቹ ወደ እኛ አካባቢ እንደመጣቹ አታስቡ፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ እንደቤተሰብ ሆኖ  እናንተን ለመንከባከብ ዝግጁ ነው” ብለዋል ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፡፡ ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በዘር፣በቋንቋ እና በመሳሰሉት ልዩነት ሳይፈጥሩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በፍቅርና በመደጋገፍ ትምህርታቸውን ሊማሩ እንደሚገባ አባ ገዳው መክረዋል፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ገለታ መረራ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርስቲው ዋናው ተግባሩ የመማር ማስተማር በመሆኑ ተማሪዎቹ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን ተከታትለው እንዲያጠናቅቁ በትምህርት ሂደቱና በአገልግሎት አሰጣጡ ያልተቋረጠ ክትትል ይደረጋል፡፡ ተማሪዎች በሂደት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከዩኒቨርስቲው ጋር ተነጋግረው በመፍታት የትምህርት ግዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ብቁ ዜጋ ሆነው እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በመቱ ዋና ጊቢና በበደሌ ካምፓስ 2 ሺህ 72 አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሏል፡፡ ዘንድሮ የተቀበላቸውን ጨምሮም  7ሺህ 670 ተማሪዎችን በ41 የትምህርት ክፍሎች በመደበኛው መርሀግብር እያስተማረ ነው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም