ለበርካታ አመታት ያለአገልግሎት ታጥረው በተቀመጡ የኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

61
ህዳር 12/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለበርካታ አመታት ያለአገልግሎት ታጥረው በተቀመጡ የኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀመረ ፡፡ እርምጃው ከተወሰደባቸው ታጥረው የነበሩ መሬቶች መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ ለ20 አመታት በሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያ ያለአገልግሎት ታጥሮ የነበረ የኢንቨስትምንት መሬት ላይ የነበረ ንብረት በዛሬው እለት  እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ከባለ ሀብቶች የተነጠቁ መሬቶች በቀጣይ ለህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲውሉ ጥናት መጠናቀቁንም የከተማ አስተዳደሩ መሬት ባንክና ማስተላለፍ ፅ/ቤት ጠቁሟል፡፡ የአስተዳደሩ መሬት ባንክና ማስተላለፍ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ጥላሁን ተስፋዬ  እንዳሉት ለአመታት መልማት ሲገባቸው ታጥረው የቆዩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቦታዎች ላይም እርምጃው እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡ ያለአገልግሎት ታጥሮ ለበርካታ አመታት የቆዩ መሬቶች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ  እንዳስደሰታቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ተክሌ ዮሃንስ እንዳሉት ይህ ሰፊ ቦታ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ለባለሃብት ተሰጥቶ ከታጠረ በኃላ  ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጥ መክረሙ ትክክል አለመሆኑን ገልፀው የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን ለልማት ለማዋል የጀመረው እርምጃ እንዳስደሰታቸው ነው የተናገሩት፡፡ የግንባታ እቃዎችን ከማስገባትና ከማስወጣት በስተቀር ምንም የሚሰራ ነገር ሳይኖር ለ20 አመታት የኖረ ነው ያሉት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ  አቶ ፍቃዱ ግርማ ናቸው፡፡ መሬቱ እስከ ዛሬ ያለአገልግሎት ሲቀመጥ እርምጃ አለመወሰዱ ትክክል እንዳልነበር ተናግረው  በቀጣይ  ከተማውን የሚመጥንና ለህዝብ አገልግሎት ለሚሰጥ ተግባር  ሊውል ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ አስተዳደር ኃላፊ  አቶ ጥላሁን ተስፋዬ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ባለሀብቶች መሬቱን ለማልማት የገቡትን ቃል  ባለማክበራቸው ነው፡፡ በከተማው  ከዚህ በፊት በድልደላ ሲሰጥ የነበረበት ሁኔታ በመኖሩ ያንን አክብሮ ለህዝብ አገልግሎት የሚሆን  ተግባር ሳይሰሩ ለበርካታ አመታት በከተማው ውስጥ ታጥረው የተያዙ ቦታዎች ላይ በህጉ መሰረት እርምጃ በመወሰድ ወደ  መሬት ባንክ የመመለስ ስራ  በከተማው ደረጃ ከዛሬ ጀምሮ መሰራት መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡ መንግስትና ባለሃብት በጊዜ ገደብ  ላይ የተመሰረተ የልማት ስራ እንዲሰራና ለህዝብ የጋራ አገልግሎት መስጫነት  እንዲውል የተሰጠ ትልቅ ሀብት እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ አስተዳደሩ ታጥረው በተቀመጡ መሬቶችና የመሬት አስተዳዳር ስራ ላይ ህብረተሰቡ  ከፍተኛ የመልካም አስተዳዳር ችግር እንደፈጠረበት  ሲያነሳ እንደነበር ገልጸው፤አዲሱ አመራርም ህግን መሰረት በማድረግ መፍትሄ ማስቀመጡን ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይም ወደመሬት ባንክ የሚገቡ ቦታዎችን ለህዝብ የጋራ አገልግሎት እንደሚያውል እና ለዚህም አስተዳደሩ ጥናት አጠናቋል ነው ያሉት፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ካቢኔ በከተማው ውስጥ  ያለአገልግሎት ለበርካታ አመታት ታጥረው በተቀመጡ  154 ቦታዎች በአጠቃላይ 4 ሚሊዮን 126 ሺ 423 ካሬ ሜትር ስፋት የኢንቨስትመንት መሬት የሊዝ ውል እንዲቋረጥ ማድረጉን መዘገባችን ይታወቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም