የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው እንዲፈቱላቸው ጠየቁ

63
ጅግጅጋ ህዳር 12/2011 የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ላሉባቸው የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አዲሱ የክልሉ አመራር ተገቢ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስተፌ መሁመድ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ትናንት ከጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ጋር መክሯል። በጎዴ ከተማ ከሚገኙ አስር ቀበሌዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን አንስተው ከምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የከተማው ነዋሪዎች ያለባቸውን የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል፡፡ በመደረኩ ከተሳተፉት አገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ቃሊብ አብዲራህማን እንዳሉት በክልሉ ላለፉት አስር ዓመታት የነበረው የቀድሞ የክልሉ አመራር በከተማው ሊጠቀስ የሚችል የልማት ሥራ አላከናወንም፡፡ "በከተማችን ያለው ዓመራርም  ቢሆን የጎላ የልማት ሥራ ቀርቆ አንድ መጸዳጃ ቤት እንኳን አልሰራልንም" ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በከተማው በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ቃሊብ አዲሱ የክልሉ አመራር አገራዊ ለውጡን ተጠቅሞ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎቻቸውን እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡ ልላው ወጣት አያን ዲርዬ በበኩሉ ዋቢ ሸበሌ ወንዝ በወጣቶች እንዲለማ አዲሱ አመራር በትኩረት እንዲሰራ ጠይቋል፡፡ እርሱን ጨምሮ የከተማው ወጣቶች በከተማው የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ ከአዲሱ አመራር ጋር በመሆን እንደሚሰሩ ተናግሯል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስተፌ ሙሁመድ በበኩላቸው እንዳሉት የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ይደርስባቸው የነበረውን በደል፣ ጭቆናና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲታረሙ ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ቀደምሲል የነበረው የአመራር ሹመት ህዝቡን ያላሳተፈ በመሆኑ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ሳይሰጣቸው መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የጎዴ ከተማ ነዋሪዎችም የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ከራሳቸው መመደባቸውን ገልጸው አመራሮቹ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት እንደሚሰሩ አመለክተዋል፡፡ አቶ ሙስተፌ እንዳሉት ላለፉት 27 ዓመታት በክልሉ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ ቆይተዋል። አዲሱ የክልሉ መንግስት ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የህግ ታራሚዎችን በይቅርታ ከመፍታት ጀምሮ ሀገራዊ የለውጥ ሥራዎችን የሚያግዙ ሥራዎች ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ አመራር በቀጣይ ከህዝቡ ጋር በመመካከር የከተማዋን ነዋሪዎች መሰረት ያደረጉ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሥራዎችን በትኩረት እንደሚያከናውንም አስረድተዋል፡፡ የጎዴ ከተማና የሸበሌ ዞን ህዝብ በዞኑ ያለው የተፈጥሮ ሀብት እንዲለማና የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ምልሽ ለመስጠት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተመራው ልዑካን ቡድን የቢርዓኖ መስኖ ግድብ ያለበትን ሁኔታ ጉብኝተዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ከቀብሪ ደሃር በነገው ዕለት ደግሞ ከደገህቡር ዞኖች ነዋሪዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና የለውጥ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል። በዚህም በዞኖቹ የሚገኙ የግብርና ኢንቨስትመንት ስራዎችና የመሰረታ ልማት ሥራዎች በመስክ ጉብኝት እንደሚደረግባቸው ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም