የሱስ መዘዝና የመከላከል ስራው - በጅማ ዩኒቨርስቲ

251
ሚፍታህ አህመድ  /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የጅማ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው በ1955 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ42 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በዘንድሮ የትምህርት ዘመንም ከጥቅምት ወር መግቢያ ጀምሮ ነባርና አዲስ ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቀቆ ወደ ተግባር ገብቷል። ዩኒቨርስቲው ምንም እንኳን ነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎችን አለም በደረሰበት የዕውቀት ደረጃ ለማስልጠን በቂ ዝግጅት ያደረገ ቢሆንም ከጊቢው ውጭ የተደቀነበት ከባድ ስጋትና ፈተና ግን ቀላል አይደለም ። በዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሂደት ፈተና እና ስጋት ተብሎ በዋነኝነት የተለየው ለሱስ አጋላጭ የሆኑ የንግድ ቤቶች ቁጥር መበራከትና ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ የመምጣት ጉዳይ ነው፡፡ ጅማ ዩኒቨርስቲ በጅማ ከተማ በሚገኙ አራት የተለያዩ ስፍራዎች የማስተማሪያ ግቢዎች ያሉት ሲሆን ከከተማዋ በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አጋሮ ከተማ አምስተኛ ግቢውን በማስገነባት ሂደት ላይ ይገኛል:: አራቱ ጊቢዎች በሚገኙባቸው ስፍራዎች የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶችን ለሱስ አጋላጭ የሚሆኑና ላልተገባ ባህሪያት የሚዳርጉ በርካታ የንግድ ቤቶች መከፈታቸው በወጣቱ ላይ አስከፊ አደጋ እንዲያንዣብብ መንስኤ ሆነዋል። በህጋዊ  የንግድ ቤቶች ሽፋንም ለሱስ አጋላጭ የሆኑት የንግድ ተቋማቱ ብዛታቸው በውል ተለይቶ ባይታወቅም በአይነት ግን ዘርዝሮ ማስቀመጥ የሚቻል መሆኑን በጅማ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍቅሩ ታፈሰ ያካሔዱት ጥናት መሰረት አድርገው ያስረዳሉ ፡፡ ቪዲዮ፣ ጫት፣ ሺሻ፣ ሀሸሽ፣ መጠጥ፣ የምሽት የጭፈራ ቤቶች፣ የጥንዶች መዝናኛ ቤቶች (በተለምዶ ካፕል ሃዉስ) ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ባለፈ በመዝናናት ምክንያት ሲኒማ ቤት፣ ባዛርና ጉብኝት ተማሪዎችን ወቅታዊ ላልሆነ የግብረስጋ ግንኙነት እንዲጋለጡ ምክንያት መሆኑ አልቀረም። በነዚህ ቦታዎች ወጣቶችን የመመልመል፣ የማላመድና በወጣቶች የመጠቀም ስራ እየተካሄደ መሆኑን በስፋት ይዘረዝራሉ። የመመልምል ተግባር በስፋት የሚከናወነው በአቻ ወጣት ተማሪዎች ሲሆን የሱስ ባህሪያትን ለማርካት አጋዥ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ወጣቶችን ኢላማ በማድረግ ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ትኩረት የሚደረገው በሴቶች፣ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውና የትምህርት አቅም ውስንነት ያለባቸው ሴት ተማሪዎች በመልማዮች እይታ ውስጥ በትኩረት ከሚገቡት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይ ጠንካራና በመልካም አርዓያነታቸው የሚታወቁትን ተማሪዎች በመጠቀም "ማንም የሚያደርገው ነው” የሚለውን መልካም ያልሆኑ የጓደኛ እና የአቻዎቻቸውን አደገኛ የማሳሳቻ ምክሮች በመለገስ የመመልመል ተግባርም ይከናወናል። ወጣት ተማሪዎች የሚመለመሉት በአብዛኛው የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ፣ ለሱሰኞች እንዲያገለግሉና ለወሲብ አገልግሎት ለመጠቀምና ሌሎች ተግባራት እንዲያከናውኑ ወደ ሱሰኝነት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጉዋቸዋል። ከምልመላ ቀጥሎ የሚመጣው ተግባር ከሱስ ጋር የማላመድ ስራ ነው ።  ተማሪዎች ጥሩ መስሎአቸው ወደ መልማዮች መረብ ሲሳቡ የሚቀርብላቸው የመጀመሪያው ግብዣ የጫት ቀምበጥ ነው ፡፡  ” በሬ ሆይ ሞኙ በሬ ሆይ ….. ” ዓይነት ይሆንና ከሱሱ ጋር ተላምደው መውጫው ይጠፋባቸዋል። ይህም ሂደት እንደመልማዮች ገለጻ መከተብ ይባላል ፡፡  መልማዮች አዲስ ተከታቢውን በሚፈለገው የሱሰኝነት ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ቡጭ (በገንዘብ መዋጮ)  እንኳን እንዲሳተፍ አያሰገድዱትም፡፡  ምክንያቱም የክብር እንግዳ የወደፊት ተስፋቸው ነው/ናትና፡፡ ተመልማዩ  በሚፈለገው ደረጃ የሱስ ተጠቂ ከሆነ በኋላ መልማዮቹ ሴጣናዊ የሆነ የሱስ፣ የፍላጎትና አለፍ ሲልም የገቢ ማግኛ ወይም መነገጃ ያደረጓቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለከፋ ሱስ የተጋለጡ ተማሪዎች የስነ-ምግባር ችግር የሚታይባቸው ከመሆናቸውም በላይ ጊዜአቸውን አልባሌ ቦታ በማሳለፍ ከተምሀርት ገበታቸው ይስተጋጎላሉ ። ማርፈድ፣ ትምህርት በአጽዕኖት አለመከታተል፣ ከመምህራን ጋር መጋጨት፣ ለጥናት ጊዜ አለመስጠት፣ የመስሰሉት ባህሪያት ስር እየሰደዱ መጥተው ጎልተው መታየት ይጀምራሉ። እንደ አጋጣሚ ተመርቀው እንኳን ቢወጡ ለአገራቸው ቀርቶ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው  ምንም የማይፈይዱ ዜጎች የመሆን እድላቸው  ሰፊ ነው፡፡ የዚህንና መሰል ችግሮች ስር መስደድ የተገነዘበው የጅማ ዩኒቨርስቲ እንደ እናትና አባት ኃላፊነት ወስዶ የተቀበላቸውን ወጣት ተማሪዎች በአጋላጭ የሱስ ባህሪያት ተደናቅፈው ከመንገድ እንዳይቀሩ በ2011 የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ተዘጋጅቷል፡፡ ዩኒቨርስቲው በዚህ ጉዳይ ላይ የ 2011ዓ.ም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ምን ያህል ከሱስ አጋላጭ ባህሪያት የጸዱ ናቸው? የመከላከል ስራው በምን ሁኔታ መሆን አለበት? እና ወደ ችግሩ ውስጥ ከገቡ በኋላስ በምን መልኩ መታደግ ይቻላል የሚሉትን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ የምርምር ስራና ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቷል፡፡ ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ አዲስ የሚገቡ ተማሪዎች ከሱስ ተጋላጭነት አንጸር በሚል ርዕስ በተጠናው ጥናት ላይ የቡድን አባል የሆኑት አቶ ማቲዎስ እንዳሉት 40 ከመቶ የሚሆኑት አዲስ ገቢ ተማሪዎች ለሱስ ባህሪ ተጋላጭነት እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት የሚያመላከት ነው፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ አዲስ በሚገቡ ተማሪዎች ላይ ባተኮረው የጥናት ግኝት መሰረት ለሱስ ተጋልጠው ከሚመጡት ውስጥ 26.3 በመቶ ጫት የሚቅሙ፣ 60 ከመቶ ደግሞ በገቡበት አመት ጫት መቃም የሚጀመሩ ሲሆኑ 31.1 በመቶ የሚሆኑት የአልኮል ልምድ ያላቸው መሆናቸውን በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን ከዩኒቨርስቲው የተገኘዉ መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህም ባለፈ አደገኛ ሱስ የሚያስይዝ ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕፅ በጅማ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥና ቆጪ በሚባለው ሰፈር እንደሚገኝ በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታዬ ቶለማሪያም ባስቀመጡት በመፍትሄ ሃሳብ  አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከአቀባበል ጀምሮ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በተለየ መልኩ መሰጠት አለበት። በተለይም የተጋላጭነት ባህሪ የሌላቸው አዲስ ተማሪዎች ከእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ጀምሮ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው አሳታፊ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ያለምንም መዘናጋት እንዲያገኙ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በግንዛቤ ፈጠራ ስራ ላይ የውስጣዊ ግፊት ምንነትን እንዲገነዘቡ መርዳት፣  በጓደኛ የመገፋፋት እና ወደ ሱስ እንዲገቡ የማግባባት ግፊት አንዳይቀበሉ መምከር ፣ ውስጣዊ ስብእና እንዲያጎለብቱ እና ማሕበራዊ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ማገዝ፣ ከሁኔታዎች ጋር የሚሔድ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ የአልኮል መጠጠን፣ የሲጋራን እና አደንዛዥ እጽን የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ጉዳቶች የማሳወቅ ሥራ መስራት፣ የትምህርት መርሃ ግብሩ ተማሪዎችን ስራ የሚያስፈታ መሆን እንደሌለበትና  የመምህራን ስነምግበርን ለተማሪዎች ጥሩ አርአያ በሚሆን መልኩ መቅረፅ የሚሉ የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀምጠዋል። በጅማ ዩኒቨርስቲ በሱስ የተያዙ ተማሪዎችን ለማከምና ከህክምና በኋላም እንዲያገግሙ የሚያስችል ማዕከል ለመክፈት የታቀደ ሲሆን ዋናው ነገር ግን ወጣት ተማሪዎች ወደ ሱስ የሚያመራቸውን ምክንያት በመለየት በፖሊሲና በህግ ማዕቀፍ የታገዘ የመከላከል ስራ ላይ  ማተኮር በአገር ደረጃ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ የሚመጡ ተማሪዎች የሱሰኝነት ባህሪን እንዳያሳድጉና ተጋልጠው የሚመጡትንም ቢሆን በማከም ከሱስ ነጻ ለማድረግ የማገገሚያ ማዕከል የማቋቋም ስራ አስፈላጊ መሆኑንም ተገልፇል። በጅማ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ በየነ ተማሪዎች ከመዝናናት ስሜት ጋር ከሚያያዙ ምክንያቶች ውጭ ትምህርት ሲክብዳቸው ወደ ሱስ የሚገቡበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ተማሪዎችን በአቅማቸው መሰረት ማስተማር፣ መደገፍ፣ መምከርና መከታተል ላይ በዘንድሮ አመት በልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አንሰተዋል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ በተለይ ሴት ተማሪዎችን እየደለሉ  ወደ ማይወጡበት የሱስ ተጋላጭነት የሚያስገቡ ወጣቶች በዩኒቨርስቲው አካባቢ እየተበራኩቱ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍም ተከታታይነት ያለው የአቻ ለአቻ የግንዘቤ መፍጠሪያና የመማሪያ መድረክ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ስለታመነበት በልዩ ትኩረት ይሰራበታል ይላሉ ። በትምህርት የአቅም ውስንነት  የሚታይባቸው ተማሪዎች በቀላሉ ለሱስ የመጋለጥና ጥንቃቄ የጎደለው የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት የሚፈፅሙበት አጋጣሚ በስፋት እንደሚታይም ተናግረዋል፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ታደሰ መጠጥ፣ ጫት፤ ሀሽሽና ሺሻ ቤት ከዩኒቨርስቲው በ500 ሜትር ክልል ውስጥ እንዳይገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ አመሽተው የሚገቡበት ሰአት ማስተካከልና  ከዩኒቨርስቲው ዕውቅና ውጭ ወጥቶ ማደርን የሚከልክል አሰራር በዩኒቨርስቲው ተገባራዊ እንዲሆን ከወዲሁ ስራ ተጀምሯል ባይ ናቸው። ለሱስ ተጋልጠው ወደ ዩኒቨርስቲ የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሚሰራበት አሰራር ትኩረት መስጠት አንዳለበትም ለፖሊሲ አውጪ አካላት በጥናት ላይ የተመሰረት ምክረሃሳብ በማቅረብ ሂደት ላይ የሚገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ወላጆች ወደ ዩኒቨርስቲ የሚልኳቸው ልጆች ከሱስ የጸዱ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት በኩል ክፍተት የሚታይ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይመክራሉ። ጅማ ዩኒቨርስቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በዋነኝነት ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከስፖርት ማዘውተሪያና ከቤተ መጻህፍት ተቋማት ጋር ተባብሮ ለመስራት መታቀዱን ከዩኒቨርሲቲው የተዘጋጁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ችግሩ የጋራ በመሆኑ መላው ህብረተሰብም ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመቆም የበኩሉን ደርሻ ሊወጣ ይገባል እንላለን። ቸር እንሰነበት ! ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም