በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በ57 ሚሊዮን ብር ወጪ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ

62
ነቀምቴ ህዳር 12/2011 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በ57 ሚሊዮን ብር ወጪ የሦስት መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩን የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በአቤ ዶንጎሮ፣ በአባይ ጮማንና ጀርዳጋ ጀረቴ ወረዳዎች የሚገነቡት ፕሮጀክቶች ከሁለት ሺህ የሚበልጡ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ በጽህፈት ቤቱ የመስኖ ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ደረጀ ኦልጅራ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ሲጠናቀቁ በአንድ ጊዜ 527 ሄክታር መሬት ያለማሉ ብለዋል። በዓመቱ ሰባት ነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥገናም በ14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተካሄደ መሆኑንም አመልክተዋል። በጅማ ገነት ወረዳ የበልበላ ሶርጎ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ ደሳሳ  በሰጡት አስተያየት መንግሥት በአካባቢያቸው በገነባው ዘመናዊ መስኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ካለሙት ቡና፣ ጫትና አፕል የተሻለ ምርትና ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ  ተናግረዋል። የጋሙ ነገሮ ቀበሌ አርሶ አደር ሙሉጌታ ጉርሜሳ በበኩላቸው በአከባቢያቸው በተገነባው ዘመናዊ መስኖ 20 አርሶ አደሮች ሆነው በማልማት ህይወታቸውን መቀየር ችለዋል ብለዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በሁለት ሄክታር መሬት ባለሙት አቮካዶ ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በልማቱ ባገኙት ትሩፋት የመኖሪያ ቤትና የበርካታ የቤት እንስሳት ባለቤት ከመሆናቸውም ባሻገር 217 ሺህ ብር ቆጥቤያለሁ ብለዋል። በሆሮ ጉድሩ ዞን ባለፉት ዓመታት ከ50 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደተገኘ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም