ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከ ኦ.ዴ.ግ አመራር አባላት ጋር ተወያዩ

57
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራር አባላት ጋር ተወያዩ። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በቲውተር ገጻቸው ባሰራጩት መልዕክት እንደገለፁት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመሳተፍ ተስማምተዋል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ሂደቱ የበለጠ እንዲሰፋ ትኩረት በመስጠት በጋራ ለመስራትም ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል። ቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ መሪ የነበሩትና አሁን ኦዴግን የመሰረቱት አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች በስደት ከሚኖሩበት ውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በትናንትው ዕለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች አገራቸው በመግባት በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ኦዴግ በቀጣይ እንደ አገር ውስጥ ፓርቲ ተመዝግቦ፣ ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመጣመር ለመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳለው አቶ ሌንጮ አዲስ አበባ ሲገቡ በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል። የአገርን ለውጥ የሚመኝ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ መታገልን ቀዳሚው ምርጫ ማድረግ እንደሚገባውም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም