የውኃ ኃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ ሙያተኞችን በስፋት ለመፍጠር እየተሰራ ነው

109
አዲስ አበባ   ህዳር 11/2011 አገራዊ የውኃ ኃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ሙያተኞችን በስፋት ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን የአፍሪካ የውኃ ማኔጅመንት የልህቀት ማእከል ገለጸ። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ያደረገው ይኸው ማዕከል የአፍሪካን የውኃ ኃብት በሚገባ ጥቅም ላይ ለማዋል ዓላማ ታስቦ ነው በዓለም ባንክ ድጋፍ የተቋቋመው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ሰፊ የውኃ ኃብት ቢኖራቸውም ይህን ኃብት በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል በመስኩ የበቃ የሰው ኃይል አለመኖሩን ጥናቶች ያስረዳሉ። ማዕከሉ በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የሰው ኃይል ክፍተት በመሙላት አገሪቷ ከውኃ ኃብቷ በአግባቡ እንድትጠቀም እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው። የማእከሉ ኃላፊ ዶክተር ፈለቀ ዘውገ እንደገለጹት ይህን ለማሳካት ማዕከሉ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በማስተርስና በዶክትሬት ዲግሪ መርሃ ግብሮች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሩዋንዳ፣ ማላዊ፣ ኡጋንዳ፣ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ ተማሪዎችን ተቀብሎ በውኃ ኃብት አጠቃቀም ቴክኖሎጂ እያሰለጠነ ይገኛል ብለዋል። ትምህርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መሰጠቱ ተማሪዎች በውኃ ኃብት ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ አገሪቱ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚስያስችል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የመስኩ ምሁራንና ሙያተኞች ወደ ሌሎች አገሮች በመላክ ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር እንደሆነም ተናግረዋል። በማዕከሉ በዋናነት የውኃ አስተዳደር፣ አጠቃቀም፣ የውሃ ንጽህና እና የውሃ ማጠራቀም፣ የውኃ ፍሳሽ አወጋገድ፣ የውኃ ብክነት፣ ውሃን መልሶ መጠቀም እንዲሁም የውሃ ሳይንስ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም