ሕዝበ ሙስሊሙ የእስልምና አስተምህሮትን መሠረት ሳይለቅ ለአገራዊ ሰላምና አንድነት እንዲሰራ ተጠየቀ

71
ድሬዳዋ/አክሱም ህዳር 11/2011 ሕዝበ ሙስሊሙ የእስልምና አስተምህሮትን መሠረት ሳይለቅ አገራዊ ሰላምና አንድነትን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የድሬዳዋ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትና የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ሸሪዓ ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረቡ። የድሬዳዋ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዑስታዝ አዩ ሐሰንና የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ሸሪዓ ጽህፈት ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሳሊሕ ዑስሌማን ዛሬ  የነቢዩ መሐመድ 1493ኛው የልደት በዓል ሲከበር እንዳስገነዘቡት ሕዝበ ሙስሊሙ የነቢዩን አስተምህሮትን ፍቅርና ሰላምን በሕይወቱ አጥብቆ በመጓዝ የአገሩንና የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ አለበት፡፡ የመከባበርና መቻቻልን እሴቶችን ለእምነቱ ተከታዮች በማስተማርና በማስቀጠል እንዲሆንም አሳስበዋል። በተለይ ወንድማማች የሆኑት የኦሮሞና የሶማሌ ወጣቶች ትዕግሥት በመላበስ መረዳዳትና አንድነትን በማጽናት ለአገራቸው ምሳሌ በመሆን የአካባቢያቸውን ልማት ዳር ማድረስ እንዳለባቸው ዑስታዝ አዩ አስገንዝበዋል፡፡ ''ወንድማማች ከተገዳደሉ በምድራዊም በሰማያዊም ዓለም ይጠየቃሉ ፤ሁለቱም ገሃነም ይጣላሉ ፤ በምድር የሚተጉለት ሰማያዊ ጉዳይ መና ይቀራል፤ ህዝበ ሙስሊሙ ይህን በመረዳት ለፍቅርና ለኅብረትና ለአንድነት መትጋት ይገባዋል'' በማለትም ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት አብዱከሪም መሐመድ እስልምና ሰላም መሆኑን ገልጾ፣ወጣቶች በሰከነ መንገድ ችግሮቻቸውን በመነጋገር መፍታት ይገባቸዋል ብሏል፡፡ ሌላው ወጣት አኒሳ አብደላ ''በሕይወቴ የምከተለው መርህ የነቢያችንን ትህትና ትዕግስት መፈቃቀርን ነው። እነዚህ እሴቶች ለድሬዳዋና ለእኛም ጭምር መልካም ቦታ የሚያደርሱ በመሆኑ ወጣቱ እነዚህን ተግባራዊ እንዲያደርግ መሥራት ይገባቸዋል'' ብሏል፡፡ የእምነቱ መምህር ወጣት ሙስጠፋ በያን ነቢዩ መሐመድ ለሕዝበ ሙስሊሙ ያስተማሩት የፍቅርና የኅብረት እሴቶችን ለትውልዱ ለማስተማር ኃላፊነቴን እየተወጣሁ እገኛለሁ ብሏል፡፡ ወጣቶች ከእርስ በርስ ግጭትና ክፍፍል ርቀው በአካባቢያቸው ሰላም፣ አንድነትና መተባበር እንዲያራምዱ የእምነቱ አባቶች ማስተማር  እንደሚጠበቅባቸውም አስተያየቱን ገልጿል፡፡ ''ወጣቶች ፊታቸውን ወደ እምነቱ በመመለስ በቅዱስ ቁርዓንና ሐዲስ የተጻፉትን የአንድነት  እሴቶች መገንዘብ ይገባቸዋል'' ብሏል፡፡ በአክሱም ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የከተማው ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካሕሳይ  በበኩላቸው እንዳሉት ለዘመናት የቆየውን የመከባበር፣የአንድነትና የሰላም ተምሳሌትነት ለማስቀጠል ማህበረሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ የከተማው ሙስሊም ማህበረሰብ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ተባብረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። የአክሱም ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሼህ ዓብደላ ሐጂ ሙስጠፋ የመውሊድ በዓል የሰላምና የአንድነትና የመከባበር ተምሳሌት መሆኑን አመልክተው፣ የተቸገሩ ወገኖች በመርዳት፣የመከባበርና የመቻቻል እሴቶች በማጠናከር መከበር እንዳለበት ገልጸዋል። የበዓሉ ተሳታፊ አብደልዓሊም ሼህ መሐመድ ከማል በሰጡት አስተያየት የአክሱም ሙስሊም ማህበረሰብ እንደተጨቆነ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ተቀባይነት የሌለውና ከማህበረሰቡ እምነትና አስተሳሰብ ውጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም