በትግራይ የሚነገሩ ቋንቋዎችን መሰረት ያደረገ አገር አቀፍ ሲምፖዝየም በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ ነው

55
መቀሌ ህዳር 11/2011 በትግራይ ክልል የሚነገሩ ቋንቋዎችን መሰረት ያደረገ አገር አቀፍ ሲምፖዝየም በመቀሌ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ተክሉ ዛሬ እንደገለፁት ከህዳር 14 ቀን 2011 ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ሲምፖዝየም ዋና አላማው በክልሉ የሚነገሩ ቋንቋዎች ስነ ልሳን፣ ስነ ቃልና ስነ ጽሁፍ እድገት ዙሪያ ለመወያየት ነው፡፡ በሲምፖዝየሙ ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቋንቋ ምሁራን አማካኝነት 24 ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ፡፡ በምሁራኑ ከሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል  17 በትግርኛ፣ አምስት በሳሆኛ እና ሁለት ደግሞ በኩናምኛ ቋንቋዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጽሁፎቹ በስምፖዝየሙ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ መግባባት የተደረሰባቸው ጥናታዊ ጽሁፎች በመጽሀፍ መልክ ታትመው ለህብረተሰቡ እንደሚሰራጩም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት አካዳሚው ባዘጋጀው ሲምፖዝየም ከቀረቡ 82 ጥናታዊ  ፅሁፎች ውስጥ 60ዎቹ በመፅሀፍ መልክ ታትመው ለአንባቢያን  መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ በሲምፖዚም 96 የሚሆኑ የዘርፉ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ተጋባዢ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም