የእንግሊዝ ኩባንያዎች በኃይል ማመንጫ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪና በመሠረተ ልማት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው

73
አዲስ አበባ ህዳር 11/2011 የእንግሊዝ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኃይል ማመንጫ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪና በመሠረተ ልማት መስኮች ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው በእንግሊዝ የአፍሪካ ንግድ ኮሚሽነር ኤማ ዌድ ስሚዝ ተናገሩ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኮሚሽነሯ የተመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በእንግሊዝ የአፍሪካ ንግድ ኮሚሽነር ኤማ ዌድ ስሚዝ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ የእንግሊዝ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አመልክተዋል። በኃይል ማመንጫ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪና በመሠረተ ልማት መስኮች የሚሰማሩ ኩባንያዎችን ቁጥር ለማሳደግም ፍላጎት አለ። ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከርና ተጨማሪ ኩባንያዎችን ወደ ኢትየጵያ እንዲመጡ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የልዑካን ቡድኑ ዓላማ የኢትዮጵያና የእንግሊዝን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል። በኃይል ማመንጫ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ በቱሪዝምና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። የፌር ፋክስ አፍሪካ ድርጅት ኃላፊ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው የንግድ ልዑካን ቡድን ውስጥ የተወሰኑት በኃይል ማመንጫ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የወሰኑ እንዳሉም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን የግል ባለሀብቱ ዋና አጋር በመሆኑ ለባለሀብቶች ምቹ አካባቢን የመፍጠር ስራዎች በተሻለ መንገድ እንደሚከናወን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መናገራቸውን ወይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ካሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች አንጻርም ለግሉ ዘርፍ ድጋፍና ማበረታቻ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል። መንግስት በሁሉም መስክ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ  ጥሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም