የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነታችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል...የድሬዳዋ ወጣቶችና ሴቶች

69
ድሬዳዋ ግንቦት16/2010 በድሬዳዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶችና ሴቶች ገለጹ፡፡ 27ኛ ዓመት የግንቦት ሃያ በዓልን አስመልክተው በተለያዩ የድሬዳዋ ቀበሌዎች የሚኖሩ ወጣቶችና ሴቶች ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በየአካባቢያቸው በትምህርት፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማትና በሌሎች ልማቶች ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶችና ሴቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም በገጠርና በከተማ የተከናወኑ ማህበራዊና፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው ለኢዜ የገለጹት። ወጣት እስክንድር ነጋ በአካባቢው እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የትምህርት ተቋማት  በመስፋፋታቸው የትምህርት እድል ማግኘቱን ገልጾ፣ በአሁኑ ወቅት ከ12 ጓደኞቹ ጋር ከመንግስት ባገኙት ተንቀሳቃሽ የገንዘብ ብድር ተደራጅተው ወደሥራ መግባታቸውን ተናግሯል። “እኔና ጓደኞቼ በተፈጠረልን የሥራ ዕድል ይበልጥ ተጠቃሚ እንደንሆን ያለብን የገበያ ችግር በመንግስት  በኩል ሊፈታን ይገባል” ብሏል፡፡ የ23 ዓመቱ ወጣት መሀመድ ጣሃ በበኩሉ ባለፉት ዓመታት ከሰላም፣ ከልማትና ከተጠቃሚነት አንጻር በአካባቢያቸው ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን ገልጿል። በቀጣይ ለአካባቢው ሰላምና እድገት መጠናከር ወጣቱን በልዩ ትኩረት በየደረጃው የማሳተፍና ተጠቃሚነቱን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል። ከመንግስት በተመቻቸለት ብድርና መስሪያ ቦታ በመታገዝ የብረታብረትና የእንጨት ውጤቶችን በማምረት በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ብር ካፒታል ለማፍራት መቻሉን የገለጸው ደግሞ ወጣት አንዱአለም ወንድወሰን  ነው፡፡ “መንግስት ላለፉት ዓመታት ወጣቶችን በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከተለ ያለው ስትራቴጂ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ መሰረት ሆኖኛል ” ብሏል፡፡ ለወጣቶች በተመደበ ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር ተጠቃሚ የሆነችው ወጣት ምንዳዬ ዮሐንስ በበኩሏ ‹‹በዕድሜዬ ሌላ መንግስት አላውቀም፤ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነት በማድጉ እኔም ሆንኩ በርካታ ሴቶች የትምህርት እድል እንድናገኙ  እንዳስቻላቸውና አሁን ደግሞ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ” ብላለች፡፡ ወጣቱ የፌደራል ሥርአቱን ጠብቆ እንዲያቆይ ከተፈለገ ተጠቃሚነቱን ከማሳደግ ባለፈ ያሉበትን የሥራ ዕድል፣ የገበያ፣ የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎች ችግር መንግስት በትኩረት መፍታት እንዳለበት ተናግራለች። በድሬዳዋ የቀበሌ 05 ነዋሪ ወይዘሮ ዝናሽ ተሰማ በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ለሴቶች በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት። "እኔ ከማጀት ወጥቼ ባገኘሁት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆኛለሁ፤ መብቴና ጥቅሜ እንዲከበርም በአደባባይ መሟገት የጀመርኩት አሁን የሴቶች መብት በመከበሩ ነው ” ብለዋል፡፡ በሀገር ልማት ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታችን እንዲጎለብት ያደረገው የፌደራል ስርአት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የበኩላቸው ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል። ወይዘሮ አሻ ሙመድ በበኩላቸው በህገ መንግስቱ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መረጋገጡ  በማንነቴ እንድኮራ፣ ባህልና ቋንቋዬን እንድንከባከብ በነጻነት ለመጠቀም አስችሎኛል” ብለዋል፡፡ ሴቶች ከግንቦት 20 ውጤቶች ይበልጥ እንድንጠቀምና በሁሉም መስክ ተሳትፏችን እንዲጎለብት ለሴቶች ተብለው የወጡ አዋጆችና ህጎች በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋላቸው በየጊዜው ክትትል እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው እንዳሉት ወጣቶችና ሴቶችን በሀገር ልማትና ዕድገት ውስጥ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተከናወኑ ተግባራት ፍሬ እያፈሩ ናቸው፡፡ በቀጣይም በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች ይበልጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በወጣቶችና ሴቶች ያሉባቸውን ችግሮች ተለይተው ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በአስተዳደሩ በኩል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም