አቶ ገዙ አሰፋ የጌዴኦ ዞንን እንዲመሩ ተሾሙ

52
ዲላ  ህዳር 11/2011 የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ  አቶ ገዙ አሰፋ ዞኑን በምክትል ዋና አስተዳዳሪነት እንደሚመሩ ሾመ፡፡ በዲላ ከተማ ዛሬ የተጀመረው የምክር ቤቱ ጉባኤ አቶ ገዙ አሰፋን የሾመው በዞኑ የደኢህዴን  ተወካይ አቶ ኢዮብ ዋቴ አቅራቢነት ነው፡፡ የድርጅቱ ተወካይ እንዳሉት አቶ ገዙ ለምርጫ ያቀረቧቸው የዞኑ ህዝብ ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች  ለመፍታት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ድርጅታቸው በማጤን ነው፡፡ የቀድሞው ዋና አስተዳዳሪ ለክልል የስራ ኃላፊነት ተሹመው በመሄዳቸው ዞኑን በምክትል ዋና አስተዳዳሪነት እንዲመሩ ምክር ቤቱ አቶ ገዙ አሰፋን በአብላጫ ድምጽ መርጧቸዋል፡፡ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበውም ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ወራሳ ተሿሚው የዞኑን ህዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፈታት ከምን ጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡ የምክር ቤቱ ጉባኤ በሶስት ቀናት ቆይታው የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2010 ክንውን በመገምገም የተያዘውን ዘመን  እቅድ  ላይ እንደሚወያይ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በምዕራብና ምሥራቅ ጉጂ ዞኖች የሚኖሩ የጌዴኦ ተወላጆችን ሰብአዊ መብት አጠባበቅ ፣ ካለው ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የጌዴኦ ዞን በክልል የማደራጀት ሀሳብንና ቀጣይ እጣፈንታን አስመልክቶ በአጀንዳነት ተይዞ ለመወያየት ምክር ቤቱ ወስኗል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም