ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላምና ልማት ቀጣይነት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

57
አዳማ/ጅማ  ህዳር 11/2011 ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና ልማት ቀጣይነት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች  አስገነዘቡ። 1ሺህ 493ኛው የነቢዩ ሙሐመድ  የመውሊድ በዓል አዳማና በጅማ ከተሞች በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ በተለይም በአዳማ ከተማ ዑሉማኢዎች፣ኢማሞችና  የእምነቱ ተከታይ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኘበት በነሽዳና በመንዙማ በተከበረበት ወቅት የከተማ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሃጂ ዑመር ከብር ሁሴን  እንደገለጹት ህዝበ ሙስልሙ በዓሉን ሲያስብ የሀገርን ሰላምና ልማት ቀጣይነትን ባረጋገጠ መልኩ ሊሆን ይገባል። "የሀገራችን እድገትና ልማት ለማቀጨጭና ሰላምን ለማወክ የሚፈልጉ ኃይሎችን ሙስልሙ ማህበረሰብ አጥብቆ ማውገዝና መታገል ይገባዋል" ብለዋል። በከተማዋ የሚኖሩ  ህዝቦች በእምነትና በጎሳ ሳይለያዩ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደ ፊት ለማራመድ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዘበዋል ። በተለይም ወጣቱ ሰላምን በማስፈንና በልማት ሰራዎች ንቁ ተሳትሮ እንዲያደርግ መክረዋል ። "ሀገር የሚገነባው፣የሚበለፅገውና ቀጣይ እጣ ፋንታው የሚወሰነው በአምራች ኃይል በመሆኑ የወጣቶች ሁለንታዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት" ብለዋል። መውሊድ ቁርዓን የተገኘበትና የሰው ልጅ  በዘር በቀለም ሳይለይ እኩልነቱ የታወጀበት እለት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጀሚአል ሀብብ መስጊድ  ኢማም  ሃጂ ከማል አህመድ ናቸው። "ቀኑን ስናስብ ለፈጣሪያችን ምስጋና በማቅረብና ስለሀገራችን ሰላም ፀሎት በማድረግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል ። በሀገሪቱ  ህዝቦች መካከል ይበልጥ መቀራራብ፣መቻቻልና መተዛዘን እንዲኖር ፣ ሰላም እንዲሰፍን ህዝበ ሙስሊሙ መንግስትን በፀሎት ማገዝ እንደሚገባው አመላክተዋል ። ከምእመናኑ መካከል አቶ ሙስጠፋ ሳይድ "በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት፣የቲሞችን በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም ሰደቃ በማውጣት እያከበርን ነው" ብለዋል ። አቶ ሙስጠፋ እንዳሉት በዶክተር አብይ አህመድ አማካይነት በህዝበ ሙስሊሙ መካከል የነበረው ክፍፍል ተወግዶ ወደ አንድነትና ጠንከራ ትስስር በተመለሰበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ከወትሮው ልዩ ያደርገዋል ። በተመሳሳይ በዓሉ በጅማ ከተማ በመድረሳ ጊቢ  በተከበረበት ወቅት የከተማው እስልምና ጉዳዮች ጽፍት ቤት ፕሬዘዳንት ኡስታዝ አህመድ መሃመድኑር ህዝበ ሙስሊሙ ዘውትር መልካም ተግባሮችን ማከናወኑን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዘበዋል። "ተወዳጁ ነብዩ ሙሃመድ በመወለዳቸው ህዝቡ ሙስሊሙ በመደሰቱ ምክንያት የመውሊድ በዓልን በየዓመቱ በጋራ እያከበርን እንገኛለን" ብለዋል "የልደት በዓሉን በደስታ የምናከብረው ነብዩ መሃመድ የክፋት፣ የምቀኝነትና የተንኮልን ጎጂነት በማስተማር የአለም ህዝብ በሰላም፣ በደስታ፣ በመተዛዝን፣ በፍቅርና በአንድነት እንዲኖር የሰበኩና ያስተማሩ በመሆናቸው ነው" ሲሉም ገልጸዋል። ህዝበ ሙስሊሙ  በዓሉን  ሲያከብር እርስ በርስ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና የሀገሪቱን  ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ሊሆን እደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ። ህዝበ ሙስሊም  በሀገሪቱ የሰላምና መረጋገት ዕጦት የሚያደረሰውን ችግር አስቀድሞ በመረዳት የድርሻውን  እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም