የራያ ዓዘቦ ወረዳ ወጣቶችን ወንጀልን የመከላከል ስራ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የማስፋት ስራ ይካሄዳል - የዞኑ ፖሊስ

81
ማይጨው ህዳር 11/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ ዓዘቦ ወረዳ ወጣቶች በማካሄድ ላይ ያሉት ወንጀልን የመከላከልና የአከባቢያቸውን ሰላምና ድህንነት የማስከበር  ስራ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የማስፋት ስራ እንደሚካሄድ የዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በወረዳው በማህበር ተደራጅተው የአካባቢ ሰላምና ደህንነት በማስከበር በጎ ተግባር የተሰማሩ 200 ወጣቶች አንድ ሺህ ለሚሆኑ የዞኑ ወጣቶች ትላንት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የህዝብ አደራጃጀትና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ሓለፎም ሓዲስ እንደተናገሩት የወረዳው ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በራሳቸው ተነሳሽነት በማህበር ተደራጅተው የጀመሩት ሰላምን የማስከበር ስራ የሚደነቅ ነው፡፡ ወጣቶቹ ወንጀልን ከመከላከል ባሻገር የትራፊክ ህግና ስነ-ስርዓትን በማስከበር ህብረተሰቡን ከአደጋ እየተከላከሉ መሆናቸውን ኮማንደሩ ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ በጸጥታ በጎ ፍቃድ አገልግሎት በተሰማሩበት ወቅት ከ60 በላይ ስለታም ቁሳቁሶች፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና አውዳሚ ፈንጂዎችን በቁጥጥር ስራ በማዋል ለፖሊስ ማስረከባቸውን ኮማንደር ኃለፎም ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹ ላደረጉት ጥረት የመሆኒ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ አባላት የመለያ ልብሶችን ጨምሮ ከ40 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ የጀመሩትን ፀጥታ የማስከበር ስራ በተሻለ መልኩ ለማከናወን በወንጀል መከላከልና ህገ-መንግስት ላይ ያተኮሩ ስልጠና መሰጠት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የዞኑ ፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ኪሮስ ገብረእግዚአብሄር ናቸው፡፡ የወጣቶችን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ በዞኑ በሚገኙ ሌሎች ሰባት ወረዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በበጎ ፍቃድ ስራ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል በመሆኒ ከተማ የሰንጋተራ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሃብታሙ ገብረ እንዳለው  በከተማው የሚታየውን የስርቆት ወንጀል ለመከላከል በራሳቸው ተነሳሽነት የፀጥታ ማሰከበሩን ስራ ከጀመሩ ከስድስት ወር በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ባለፊት ስድስት ወራትም በከተማው በስርቆት ወንጀል የተጠረጠሩ 40 ሰዎችን ለህግ ማቅረባቸውን ገልጿል፡፡ የአካባቢያቸውን ደህንነት በማስጠበቅ ከተማዋን ሰላማዊ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የገለፀው ደግሞ ሌላው የማህበሩ አባል ወጣት ሓጎስ ነጮ በርሀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም