በደብረ ብርሃን ከተማ 52 የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

111
ደብረብርሀን ህዳር 11/2011 በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ 52 የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ዛሬ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት 51 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎችና  አንድ መትረየስ የተያዙት ሌሊቱን ወደ ከተማዋ ሲገቡ ነው። የሠሌዳ ቁጥር  ኮድ 3 ኢት 94012 በሆነ የጭነት መኪና ሲጓጓዙ የተያዙት መሣሪያዎች  በልዩ ሁኔታ በተሰራ ሳጥን ተቀምጠው መገኘታቸውንም አስረድተዋል። አሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ጉዳዩ  በመጣራት ላይ መሆኑንም አቶ ካሣሁን ገልጸዋል። መሣሪየዎቹ በኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ክትትል መያዛቸውንም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብርም  ኃላፊው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም