በሩብ ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላከ ሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት 27 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

53
አዳማ ህዳር 11/2011 በዘንድሮው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ ሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት 27 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃይለስላሴ ወረስ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የበጀት ዓመት 190 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዶ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ርበረብ እየተደረገ ነው፡፡ በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላከ ሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት 27 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። የሩብ ዓመቱ አፈፃፀም የእቅዱ 60 በመቶ መሳከቱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለእቅዱ አፈፃፀም ማነስ በአቅርቦት ችግር ምክንያት የኤክስፖርት ቄራዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ባለመቻላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ''በብዛት ወደ ውጭ እየላክን ያለነው የበግና የፍየል ሥጋ ነው 'ያሉት አቶ ሃይለስላሴ' በአሁኑ ወቅት በቀን ከ300 ቶን በላይ ሥጋ ማምረት የሚችል 'አለና' ዘመናዊ የኤክስፖርት ቄራ ወደ ሥራ በመግባቱ ዓመታዊ እቅዳችንን ለማሳካት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርልናል'' ብለዋል። በሥራ ውስጥ የሚገኙ 14 የኤክስፖርት ቄራዎች ባለፉት ሶስት ወራት 7 ሺህ ቶን ሥጋና የሥጋ ተረፍ ምርቶችን ወደ ተለያዩ የመካክለኛው ምስራቅ ሀገራት መላካቸውንም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ  በመስከረምና ጥቅምት ወራት የሥጋ እንስሳት አቅርቦት በእጅጉ በመቀነሱና የሀገር ውስጥ ዋጋ በመናሩ የኤክስፖርት ቄራዎች የአቅርቦት ችግር እንዳጋጠማቸው  አመልክተዋል። ''በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት ከግብርና እንስሳት ሀብት ሴክተር ተቋማት፣ ከንግድና ገበያ ልማት ዘርፎችና ከኤክስፖርት ቄሬዎች ጋር የጋራ እቅድ አውጥተን ወደ ሥራ ገብተናል' ያሉት አቶ ሃይለስላሴ 'በዚህም ዓመታዊ እቅዳችን እናሳከለን'' ብለዋል። በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይተሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ በበኩላቸው  ሀገሪቱ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ ብትይዝም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ''ሀብቱ ቢኖረንም የሀገራችን የእንስሳት አረባብ፣ አያያዝና እንክብካቤ አሰራርና ሥርዓት የምርቱን ተቀባይ ሀገራት ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ እየቀረበ አይደለም'' ብለዋል። የአቅርቦት እጥረትና የጥራት ጉድለት በዘርፉ የሚታይ ቁልፍ ችግር መሆኑንም  ተናግረዋል። ሀገሪቱ ከዘርፉ ለማግኘት ያቀደችውን 198 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል፡፡ ''በአሁኑ ወቅት የአቅርቦት እጥረቱን ለማቃለል የእንስሳት አቅራቢ ማህበራት በብዛት አደራጅተን ወደ ዘርፉ ለማስገባት ከክልል መንግስታትና በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን'' ብለዋል። በዘላቂነት ግን የኤክስፖርት ቄራዎች በሥጋ እንስሳት እርባታ ልማትና ማድለብ ጭምር ፈጥነው እንዲገቡና የአቅርቦች ችግሮቻቸውን በራሳቸው ማቃለል እንዲችሉ መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም