በአስተዳደሩ በሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እንዲያደርጓቸው ነዋሪዎች ጠየቁ

53
ድሬዳዋ ህዳር 11/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር በመገንባት ላይ በሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ሆነ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እንዲያደርጓቸው የመልካ ጀብዱና አካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ። ነዋሪዎቹ ፕሮጀክቶቹ  ሲጠናቀቁ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ የመልካ ጀብዱ ከተማና የገደንስር ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በአስተዳደሩ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የመንገድ ፕሮጀክቶች ለነዋሪዎች አንዳችም የሥራ ዕድል አለመፍጠራቸው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ልማትና ዕድገት ጠቀሜታ ያላቸው ቢሆንም፤ ለነዋሪዎች ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚ አለማድረጋቸው ብለዋል። የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ሲጀምር  ወጣቶች ሥራ እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ የገደንስር ገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ አብዱላሂ ጅብሪል በአስተዳደሩ በፌዴራል መንግሥትና በቻይና የግል ባለሀብቶች ለሚገነቡት ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የእርሻ መሬታቸውን የለቀቁት የተሻለ ልማት ለአካባቢያቸውና ለልጆቻቸው ይመጣል በሚል ተስፋ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የመልካ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጁሃር መሐመድ በአካባቢው በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ነዋሪዎች ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሁኔታ ለመቀየር አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ ''የሚጠቀሙት  የአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ነው፤ ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ከዚህ ሃብት እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል'' ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ወጣት አህመዲን አልዪ በበኩሉ ለአካባቢው ወጣቶች በፓርኮችና በመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ ሊያገኙ ይገባ እንደነበር አመልክቶ፣ አስተዳደሩ በቀጣይ ይህንን እንዲያስተካክለው ጠይቋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን የነዋሪዎቹን ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን አምነው፣ችግሩ የተከሰተው ለጉዳዩ ትኩረት ባለመሰጠቱ እንደተፈጠረ ገልጸዋል። በፌደራል መንግሥት ተገንብቶ በቅርቡ አገልግሎት በሚጀምረው የኢንዱስትሪ ፓርክ  40 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ሥራ ይፈጠርላቸዋል ብለዋል፡፡ የመልካ ቀበሌ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ መስኮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስረድተዋል፡፡ የአስተዳደሩ ወጣቶች ያለባቸውን የሥራ አጥነት ችግር ትርጉም ባለው መንገድ የሚፈቱ ሌሎች ፕሮጀክቶች እየተገባደዱ መሆናቸው ከንቲባው አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም