አዴፓ የክልሉን ህዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ

75
ባህርዳር ህዳር 11/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ የክልሉን ህዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ እንደሚሰራ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ። ድርጅቱ የተመሰረተበትን 38ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው  የክልሉን ህዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ተግባር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክና ኃላፊነት ጠንክሮ ይሰራል። " የምስረታ በዓሉን በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ ላይ ሆነን የምናከብረው ሀገራችን  በህዝብ ግፊትና በድርጅታችን ሳቢነት ተለኩሶ በተቀጣጠለው የለውጥ ፋና ውስጥ በገባች ማግሥት በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል "ብሏል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምስረታ በዓሉን የሚያከብረውም እንደ ንሥር ታድሶ ያለፈባቸውን የትግል ምዕራፎች እና አዲሱን የለውጥ ጎዳና በመቃኘት መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡ በ38 ዓመታት የትግል፣ የድልና የተግዳሮት ጉዞ ከሌሎች ዴሞክራሲያዊያን ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ የሀገሪቱን የዕድገት ትንሣኤ ለማብሠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ የማይተካና ቁልፍ ሚና መጫወቱን ገልጿል፡፡ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥር እንዲሰድም ድርጅቱ የአንድ ጎልማሳ እድሜ ያህል የትግል ጊዜ ማሳለፉን ጠቁሞ በየጊዜው የሚገጥሙትን ፈተናዎችም በብቃት እየተሻገረ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንደበቃም ገልጿል፡፡ ድርጅቱ የክልሉን ህዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ተወላጆችን መብትና ጥቅም የማስጠበቅ እና የማረጋገጥ ስራ ቀድሞ የነበሩ ችግሮችን በሚፈታ መንገድ ለማከናወን እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ "ከወሰንና ከማንነት ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚነሱትን ጥያቄዎች የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንዲፈቱ በኃላፊነት መንፈስ ይሰራል" ብሏል ድርጅቱ በመግለጫው፡፡ " የተገኘውን ለውጥ እየገሰገሰ ካለበት ሀዲድ እንዳያፈነግጥ በብቃትና በቆራጥነት መምራት እና መግራት ወቅቱ የሚጠይቀን የጋራ የቤት ሥራ መሆኑን ድርጅቱ ያምናል፤ ይህን ለማስቀጠልም በጽኑ ይቆማል፤ መሥዋዕትነትም ይከፍላል" ብሏል፡፡ እንደመግለጫው የለውጥ ሐዲዱ ፍጥነቱንና ደኅንነቱን ጠብቆ  መገሥገሥ እንዲችል የድርጅቱ አባላትና መላው የክልሉ ሕዝብ፣ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ በተለያየ መልክ ዜጎች እንዲፈናቀሉና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመሩ የሚያደርጉ ተግባራት በፍጥነት መታረም አለባቸው ብሎም ያምናል ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴው፡፡ የተረጋጋ ሀገራዊና ክልላዊ ድባብ እንዲኖር በማድረግ ረገድም የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች ሁሉን ባሳተፈ ሁኔታ እንዲከናወን አዴፓ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡ የሕዝብን ሰላም በማናጋት፣ ከልማት ተጠቃሚነትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጎዳና የሚያወጡ ስሜታዊ፣ ዕብሪታዊና ጅምላዊ አካሄዶችን በጽኑ እንደሚያወግዝ ማዕከላዊ ኮሚቴው አመልክቷል፡፡ ለውጡን ለማሳካት ድርጅቱ በጽናት በመታገል የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቋል። ድርጅቱን ምስረታ አስመልክቶ ትናንት የወጣውን ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡ 38 ኛውን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምሥረታ በዓል  በማስመልከት ከአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ የተከበራችሁ የክልላችንና የሀገራችን ሕዝቦች የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች ከሁሉም በማስቀደም ለ38ኛው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምሥረታ በዓል እንኳን አደረሰን፤ አደረሳችሁ፡፡ ሠላሳ ስምንተኛው የምስረታ በዓላችን በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ ላይ ሆነን የምናከብረው ነው፡፡ ይህ የምስረታ በዓል ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕዝብ ግፊትና በድርጅታችን ሳቢነት ተለኩሶ በተቀጣጠለው የለውጥ ፋና ውስጥ በገባች ማግሥት መከበሩ የተለየ ያደርገዋል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 38ኛ የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው እንደ ንሥር ታድሶ ያለፈባቸውን የትግል ምእራፎች እና አዲሱን የለውጥ ጎዳና በመቃኘት ነው፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በ38 ዓመት የትግል፣ የድልና የተግዳሮት ጉዞ ከሌሎች ዴሞክራሲያዊያን ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ የሀገሪቷን የዕድገት ትንሣኤ ለማብሠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ወሳኝ፣ የማይተካና ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥር እንዲሰድና መሠረተ ፅኑ እንዲሆን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአንድ ጎልማሳ እድሜ ያህል ታግሏል፡፡ በየወቅቱ የሚገጥሙትን ፈተናዎችም በብቃት እየተሻገረ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የትናንት ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ የዛሬና የነገም እንጂ፡፡ የትናንት እንደመሆኑ በዚህች ሀገር የክብር መዝገብ በወርቅ ቀለም የሚጻፍ፤ ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ያደረገው የትግል ታሪክ አለው፡፡ የዛሬ በመሆኑም አሁን የምናየው አዲሱ ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄ እንዲቀጣጠልና ዳር እስከ ዳር የተስፋ ችቦ እንዲለኮስ የበኩሉን ታሪካዊ ሚና ተወጥቷል፡፡ የነገ እንደመሆኑም ኢትዮጵያን መልሶ ታላቅ የማድረግ ራእይ ሰንቆ በተተኪው ትውልድ ልብ ውስጥ እየበቀለ ነው፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የ38ኛ የምሥረታ ዓመት በዓሉን የሚያከብረው ከትናንት ታሪኩ ይዟቸው የመጣውን የድርጅቱን የጽናትና የስኬት ምስጢሮች አሁን ከተቀጣጠለው የለውጥ ጉዞ ጋር በማጣጣም ነው፡፡ የነገ ፓርቲ እንደመሆኑ ሦስት ሕዝባዊ ኃላፊነቶች ከፊቱ አሉ፡፡ የመጀመሪያው ቀድመን የጀመርናቸውን የክልሉን ሕዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ኃላፊነትና ተግባር ወቅቱ በሚጠይቀው መጠን መፈጸም ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከክልል ውጭ ያሉ ተወላጆችን መብት የማስጠበቅ እና የማረጋገጥ ተግባራትን ቀድሞ የነበሩ ችግሮችን በሚፈታ መንገድ ለማከናወን መቻል ነው፡፡ ሦስተኛው ከወሰንና ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ጥያቄዎች የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንዲፈቱ በኃላፊነት መንፈስ መስራት ነው፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሦስቱንም ጉዳዮች በሚገባቸው ደረጃና በሚጠይቁት የመሥዋዕትነት መጠን ለማከናወን ቆርጦ ተነሥቷል፡፡ የተከበራችሁ የክልላችንና የሀገራችን ሕዝቦች የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአማራ ብሄርተኝነት እና የኢትዮጵያ አንድነት ይበልጥ እንዲያብብ በቁርጠኝነት ይታገላል፡፡ ብዝኃነትን ከአንድነት፣ አንድነትንም ከብዝኃነት ያስተባበረ ሀገር ለመመሥረት አበክሮ ይሠራል፡፡ በተለይም በ12ኛው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ድርጅታዊ ጉባኤ እና 11ኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ተግባራዊ ለማድረግ በምሥረታ በዓሉ ላይ ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ እየተረባረበ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተጀመረውን ለውጥ ሳይጨናገፍ እንዲቀጥል፣ የሰላም ግንባታው ለውጤት እንዲበቃ፣ የዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩም የበለጠ እንዲሰፋ ያለማወላወል መሥዋዕትነትን ይከፍላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕዝቡ የዕለት-ከዕለት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የደኅንነት ቀውስ የሚያስከትሉ ችግሮችን በመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ረገድ በትዕግስት እና በማስተዋል የመፍትሄ አካል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የክልላችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ኢኮኖሚ በማዘመን ማነቆዎችን ፈትቶ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ የመዋቅራዊ ለውጡ ዋነኛ ዐቅም የሆነውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሙሉ ኃይሉ እየተረባረበ ነው፡፡ የማኅበራዊ አገልግሎቶች እና የመሠረተ ልማት ሥራዎቻችንን በጥራት የመፈጸም፤ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ የላቀ የርብርብ ማዕከል ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ አሁን ባለንበት የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ሆነን እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ድሎች በብቃት በመጠበቅ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ከመቼውም የላቀ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከዚህ አኳያ ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች በሚያግባባው ተስማምቶ፤ በሚያለያየው ተከባብሮ የትግል አንድነቱን ከምን ጊዜም በላይ በማጠናከር መጪው ትውልድ ድህነትን በትግል አሸንፎ በነጻነትና በኩራት የሚኖርባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት አበክሮ ይሠራል፡፡ በዚህ ወቅት ሀገራችንም ሆነ ክልላችን በሁለት ነገሮች መካከል ይገኛሉ፡፡ አንደኛው ሀገሪቱ ለዘመናት ስትጠብቀውና ስትታገልለት የቆየችው የለውጥ ጉዞ አጓጊ በሆነ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ይህንን ቡቃያ ለውጥ ለማጨናገፍ በሚኳትን ኃይል የሚወረወር ፈተና እየተከሠተ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለውጡን ከሚገሠግስበት ሐዲድ ፈጽሞ እንዳያፈነግጥ በብቃትና በቆራጥነት መምራት እና መግራት ብርቱ ርብርብ የሚጠይቀን የጋራ የቤት ሥራ መሆኑን ያምናል፡፡ በጽኑ ይቆማል፤ መሥዋዕትነትም ይከፍላል፡፡ የለውጡ ባቡር በተገቢው ሐዲድ ፍጥነቱንና ደኅንነቱን ጠብቆ ለመገሥገሥ እንዲችል የድርጅቱ አባላትና መላው የክልሉ ሕዝብ፣ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን አበክሮ ይገልፃል፡፡ በተለያየ መልክ ዜጎች እንዲፈናቀሉና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመሩ የሚያደርጉ ተግባራት በፍጥነት መታረም አለባቸው፡፡ የተረጋጋ ሀገራዊና ክልላዊ ድባብ እንዲኖር በማድረግ የተጀመሩትን የሪፎርም እንቅስቃሴዎች ሁሉን ባሳተፈ ሁኔታ አዴፓ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የሕዝብን ሰላም በማናጋት፣ ሕዝባችንን ከልማት ተጠቃሚነትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጎዳና የሚያወጡ ስሜታዊ፣ ዕብሪታዊና ጅምላዊ አካሄዶችን በጽኑ እያወገዝን በማናቸውም መልኩ ድርጊቶቹንና የድርጊቶቹ ፈጻሚዎች የማንታገሥ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡ ለውጡ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ውስጥ ተንጸባርቆ የእያንዳንዱን ቤት በር እስኪያንኳኳና የእያንዳንዱን ዜጋ መሶብ እስኪሞላ ድረስ በጽናት እንታገላለን፡፡ ባለፉት ዘመናት የተስተዋሉ የአድልዖ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ዝርፊያና ብልሹ አሠራሮች፣ ትውልድ የማምከንና ሀገር የመግደል አካሄዶች በፍጥነት ታርመው፣ ሕዝብ የሚደመጥበት፣ ፍትሕ የሚነግሥበት፣ ዴሞክራሲ የሚሰፍንበትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን የሚሆንበት ሥርዓት ለመገንባት በቆራጥነት ከፊት እንቆማለን፡፡ ባለፉት ዘመናት የተከሠቱ የተዛቡ ትርክቶች በተገቢው መንገድ ታርመው፤ ሕዝቦች በይቅርታና በዕርቅ መርሕ ወደ አዲሲቱ ኢትዮጵያ ተሻግረው፤ ሀገራቸውን ለመገንባት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ዐቅማችንን ሁሉ አሟጠን እንሠራለን፡፡ ሀገር የምንገነባው የትናንቱን በጎ ሥራችንንና ታሪካችን መሠረት አድርገን፣ እኛ በምንመዘንበት የዛሬው ሥራችን ላይ ቆመን፣ የነገውን በሚገባ ተልመን በመሥራት ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝባችን ታሪክ፣ቅርሶች፣ በጎ ዕሴቶች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የኩራቱ ምንጭ የሆኑ ባሕላዊ ክዋኔዎች በተገቢው ደረጃና መንገድ እንዲጠበቁ፣ ለሕዝቡ ጥቅም እንዲውሉና ለትውልድም እንዲተላለፉ ከማንኛውም ጊዜ በተሻለ ተገቢው ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ማንም ኢትዮጵያን ብቻውን አልመሠረታትም፣ ወደፊትም ብቻውን አይገነባትም፡፡ ምንም እንኳን የተለያየ ርእዮተ ዓለምና አሠራር ቢኖረንም፣ የምንሠራው ለአንዲት ሀገርና ለአንድ ሕዝብ እስከሆነ ድረስ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ከማናቸውም ወቅት በላቀ ዝግጁነት ላይ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን፡፡ ውድ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች መላው የሀገራችን ሕዝቦች ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት ከተመዘገቡት ድሎች በላይ ትልቁ ትምህርት ሕዝብ ያመነበትን እና ሕዝብ የፈቀደውን መሠረት አድርጎ መወስንና መፈጸም ትልቅ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተጀመረው ለውጥ በእጅጉ ተስፋ የሚሰጥና ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ያምናል፡፡ ይህ ለውጥ ቀጣይ፣ የተሟላና ከችግሮች ፈጥኖ የሚወጣ እንዲሆን ከተሠራው ያልተሠራው እንደሚበልጥ ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ወቅቱ በሁሉም መስኮች የተሟላ የተግባር ንቅናቄ የምናደርግበት ጊዜ መሆኑን በማሥመር በተሻለ ውጤታማነት ሕዝቡን ለማርካት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይህንን ለውጥ በጥራትና በፍጥነት ለማስቀጠል የለውጥ ዐቅሞችን ይዞ ለላቀ ድልና ስኬት ዝግጁ መሆንን እያረጋገጠ መላው የክልላችን ሕዝቦች፣ ከክልሉ ውጭ የምትገኙ የክልሉ ተወላጆች፣ በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንት የተሳተፋችሁ የልማት አጋሮች፣ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ እኅት ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች በሙሉ ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሃሳብ ልዕልና በለውጥ ጎዳና! ኅዳር 2011 ዓ.ም  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም