የትግራይ ህዝብ ዋነኛ አጀንዳ ድህነትን መታገል ነው---ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

82
መቀሌ ህዳር 10/2011 የትግራይ ህዝብ ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያልፍም ከዋነኛ ጠላቱ ከድህነት እስኪወጣ ድረስ ከትግሉ ወደ ኋላ እንደማይል የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ እየተከፈቱ ያሉ መንገዶች ለሁለቱም ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ አስታውቀዋል። ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የትግራይ ህዝብ ያለመውን ነገር ለማሳካት በርካታ ውጣውረዶችን አልፏል። "አሁንም ጠላታችን ድህነት ነው" ያሉት ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ "ይህ ህዝብ ከድህነት እስኪወጣ ድረስ በማንኛውም ምክንያት ወደ ኋላ የምንልበት ነገር የለም።" ብለዋል ለዚህም “የትግራይ ህዝብ አጀንዳ አሁንም ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና ድህነትን የመዋጋት ስራ ቀጣይ መሆኑ ነው” ብለዋል። በተለይም በማንነትና በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ሽፋን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የክልሉን ህዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር የማረጋገጥ አጀንዳ ለማስቀየር መሆኑን ተናግረው ህዝቡ ይህን አውቆ በትእግስትና በሰከነ ሁኔታ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው አሳስበዋል። "የትግራይ ህዝብን ለማሸማቀቅና ለማንበርከክ  ከውጭና ከውስጥ የሚደረግን ጥረት አሁንም እንደወትሮው አንድነቱን በማጠናከር ይመክተዋል" ብለዋል። "ከውጭም ከውስጥም በርካታ ሃይሎች አሉ" ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፣"ዛሬም እንደጥንቱ አንድነቱን በማጠናከር ሊመክተውና ሊከላከለው ይገባል" ብለዋል። የትግራይ ህዝብ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት በፍጹም ወደ ጦርነት እንደማይገባም በአጽንኦት ገልጸዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ሰላምና መልካም ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በፌዴራልና በክልሉ መንግስት እየተሰራ መሆኑንም  አስታውቀዋል። የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱም በኩል ፍላጎት እንዳለ ገልጸው "ይህን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ሁለቱንም ሀገራት በሚያገናኙ መንገዶችና አዋሳኝ አካባቢዎች የተከፈቱት በሮች ተጠናከረው ይቀጥላሉ" ብለዋል። አገናኝ መንገዶቹን ለሁለቱም ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ትስስር ለማዋል እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። "በሁለቱም ሃገራት ህዝቦች መካከል የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል" ያሉት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ግንኙነቱ ከዚህ በላይ እንዲቀጥል ተከታታይ ስራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም