ፖሊሲ የሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ክስን ለማጣራት የጠየቀውን የ14ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ

57
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትን ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ክስ ለማጣራት ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ። የፍርድ ቤቱ ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ/ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውን የክስ ጉዳይ ዛሬ ሲመለከት ውሏል። ፖሊሲ የሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ተጠርጥረው የተያዙበትንና የተከሰሱበትን ወንጀል ዝርዝር ለችሎት በንባብ ካቀረበ በኋላ ተጠርጣሪው በስራ ኃላፊነት ላይ በሆኑበት ወቅት በርካታ የሕዝብና የመንግስት ንብረት አለአግባብ እንዲባክን አድርገዋል ብሏል። ተከሳሹ  የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር በነበሩት ወቅት አግባብ ያልሆነ  የአውሮፕላኖች ፣ መርከቦች ፣ ሆቴሎችና ሌሎች ግዥዎችን ያለጨረታ በመስጠት ሃብት እንዲባክን አድርገዋል። በተጨማሪም በድርጅቱ ሥር ባሉ 15 ያህል እህት ኩባንያዎች አማካኝነት ከፍተኛ የመንግስትና ህዝብ ኃብት እንዲመዘበርና አለአግባብ እንዲባክን በማድረግ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ነው የተባለው። የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው ሜቴክን በሚያስተዳድሩበት ወቅትም ሆነ ከወንድማቸው ከአቶ ኢሳያስ ዳኝ ጋር በምንም አይነት በሙስና ወንጀል የሚያስከስሳቸው ተግባር አልፈፀሙም ሲል ተከራክረዋል። የዋስትና መብታቸው እንዲከበርም ጠበቃው ጠይቀዋል። በተጨማሪም ከሳሽ ወገን በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይን በመገናኛ ብዙሃን በማስተላለፍ በፍርድ ሒደቱ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ በመሆኑ "ይሕ አካሔድ እንዲቆም ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥልን" ሲሉም ጠይቀዋል። ፖሊስ በበኩሉ "ተጠርጣሪው ላይ አሁንም መረጃ እየሰበሰብኩ ነው፤ በርካታ ምስክሮችም ያሉኝ በመሆኑ ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ መረጃ የሚያጠፉ በመሆናቸው ዋስትና ሊሰጣቸው አይገባም" በማለት ተከራክሯል። የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤትም ፖሊሲ ያቀረበውን 14ቀን ተጨማሪ የምርመራ  ጊዜ ተገቢ መሆኑን አምኖበት ለሕዳር 14ቀን 2011 ቀጠሮ ይዟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም