አፍሪካ ለሩዝ ልማት የሚውል 130 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖራትም፤ያለማችው ከ10 ሚሊዮን ሄክታር አይበልጥም

119
ባህር ዳር ህዳር 10/2011 አፍሪካ ለሩዝ ልማት የሚውል 130 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖራትም፤እስካሁን ያለማችው ከ10 ሚሊዮን ሄክታር እንደማይበልጥ ዓለም አቀፍ የሩዝ ተመራማሪዎች ገለጹ። አህጉሪቱ በየዓመቱ በአማካይ 67 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ለሚገባ ሩዝ  ግዢ ታወጣለች። ዓለም አቀፍ የሩዝ ባለሙያዎችና የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች በአማራ ክልል ፎገራ ወረዳ በሩዝ ምርትና በአህጉሪቱ ሥነ-ምህዳር ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎቻቸውን እያቀረቡ ነው። የአፍሪካና የደቡብ እስያ አገሮች የሩዝ ምርምር ማዕከል ተመራማሪ ዶክተር አብደልባጊ እስማኤል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት አህጉሪቱ በሩዝ ለመሸፈን ከምትችለው መሬት የሸፈነችው 13 ከመቶውን ብቻ ነው። ልማቱ በተለመዱ የሰብል ዓይነቶች ላይ በተለይም በጥራጥሬ ትኩረት ተደርጎ ከመከናወን እንዳልወጣም አመልክተዋል። አህጉሪቱ ለሩዝ ተስማሚነት ያለው መሬት ቢኖራትም፤በተፈጥሮ የታደለችውን ፀጋ በደንብ ካለመገንዘብ ለልማቱ ትኩረት አለመስጠቱንም የሚያስረዱት ተመራማሪው፣አፍሪካውያን ሩዝን የመመገብ ባህላቸው እያደገ ከመምጣቱ አኳያ ለልማቱ ትኩረት እንዲሰጡት ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ። አህጉሪቱ የራሷን ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነውን ሥነ-ምህዳርና የአየር ፀባይ በአግባቡ ብትጠቀምበት የራሷን ፍላጎት ከመሸፈን ባለፈ፤ ለሌሎች አህጉሮች የሚተርፍ ምርት ባለቤት ለመሆን ትችል እንደነበር አመልክተዋል። ሩዝ በአግባቡ ካለሙት በሄክታር አስከ 50 ኩንታል እንደሚገኝበትና የበልግ ዝናብና መስኖን በመጠቀም በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት እንደሚቻልም አስረድተዋል። አህጉሪቱ ምርቱን የምታስገባው ከእስያ አገሮች እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር እስማኤል፣ ለምርቱ ባላት ምቹነት፣ ስፋትም ሆነ ምቹነት ብልጫ እንዳላት ይገልጻሉ። አፍሪካ በምርቱ ራሷን እንድትችል የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችንና፣ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወጣቱን አደራጅቶና አስልጥኖ ማሰማራት  ያስፈልጋል ይላሉ። በዘርፉ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮች ካልተፈቱ ለመሠረተ ልማት፣ለጤናና ለትምህርት አገልግሎት የሚውለውን በጀት ለሩዝ ግዢ እያዋለች መቀጠል እንደሌለባት ዶክተር እስማኤል ያመለክታሉ። አህጉሪቱ የዜጎቿን የሩዝ ፍላጎት ለማሳካት በዓመት 67 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች። ኢትዮጵያም በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች ብለዋል። የአፍሪካ የግብርናው ዘርፍ ምሁራን አህጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ እንድትጠቀም የማያደርጉት ከአርሶ አደሩ ጋር ስለማይሰሩ ነው ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ሩዝ ምርምር ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ፓውል ኬፕ ናቸው። አህጉሪቱ ያላትን እምቅ ሃብት በመጠቀም አርሶ አደሩን በማስተባበርና በዘርፉ አዋጪነት መጠቀም ባለመቻሉ ነው ይላሉ። ሩዝ በዓለም ላይ የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ሰብሎች ከቀዳሚዎች ተርታ እየተሰለፈ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው አፍሪካ  ሩዝ የማምረት አቅሟን በአግባቡ ብትጠቀም፤ በመግዛት ሳይሆን በመሸጥ ደረጃ ቀዳሚዋ መሆን ትችላለች ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አርሶ አደሩን በማደራጀት፣በማሰልጠንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው በማቅረብ ምርታማነቱን ለማሳደግ ያስችላል የሚሉት ዶክተር ኬፕ፣ለዚህም ተነሳሽነት፣ትምህርት መስጠትና አዋጪነቱን እንዲገነዘብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ ለምርቱ ያላትን ተስማሚ የሆነ መልክዓ ምድር በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉት አገሮች አንዷ ናት። የመጀመሪያውን ብሄራዊ የሩዝ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ከ200 ሚሊዮን በላይ በሆነ ብር ወጪ አስገንብታ ሰሞኑን በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ አስመርቃለች። የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ዑርጌሳ ማዕከሉ የአርሶ አደሩን የአስተራረስ ዘይቤ ለማዘመንና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማውጣት መቋቋሙን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለሩዝ ምርት አመቺነት ያለው ሥነ -ምህዳር ባለቤት ብትሆንም፤ነገር ግን ዘርፉ ባለመዘመኑ በዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ምርቱን እንደምታስገባ አስታውቀዋል። አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ለማስቀረትና ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እየሰራች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዘርፉን ለማገዝና ለማዘመን የግል ባለሃብቶችና ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለሩዝ ተስማሚ የሆነ መሬት ቢኖራትም፤ በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ከውጭ እንደምታስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም