ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የጤና ዲፕሎማሲን ለመተግበር የሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች

60
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011  ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም /UNAIDS /ዓለም አቀፍ የጤና ዲፕሎማሲን ለመተግበር የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የፕሮግራሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማይክል ሲድቤን ዛሬ  ተቀብለው አነጋግረዋል። በዚህ ወቅት ዶክተር ወርቅነህ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ  ''የአገራት ትብብር በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  ወሳኝ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የጤና ዲፕሎማሲን ትደግፋለች።'' አገሪቷ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ለመከላከል እያደረገችው ላለው ጥረትና ላስመዘገበችው ውጤት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራምና የሌሎች አገራት ድጋፍ  ከፍተኛ እንደነበርም ተናግረዋል። በተለይ በሽታውን ለመግታት  በውስን ሃኪሞችና በተናጥል ጥረት ውጤት ማምጣት ስለማይቻል የበሽታውን ስርጭት ለመግታት አገራት በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል፤ ኢትዮጵያም ለዚህ ዝግጁ ናት ብለዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል በምትሰራው ስራ ድርጅቱ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጠል ዶክተር ወርቅነህ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት በመሆኑ፣ ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱባትና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ቀድሞ መከላከል ላይ አተኩራ ትሰራለችም ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም /UNAIDS/ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማይክል ሲድቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያደረገችውን ቁርጠኛ አቋም አድንቀዋል። በቀጣይም ስርጭቱን ለመከላከል ተቋሙ የያዘውን የጤና ዲፕሎማሲ ከግብ ለማድረስ ኢትዮጵያ በጋራ እንድትሰራ ጠይቀው መስማማት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። የኤች.አይ.ቪ ጉዳይ የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም የኢኮኖሚም ጉዳይ በመሆኑ እየተተገበረ ላለው  የጤና ዲፕሎማሲ ዘውግ ጉዳይ የአገራት ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያም እየተገበረችው ያለውን የጤና ፖሊሲ አለም አቀፍ የጤና ዲፕሎማሲ ትልቅ ድጋፍ እንደሚሆንለትም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም