የመልካ ሶር እሬቻ በዓልን በተሻለ የህዝብ ተሳትፎ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

72
መቱ ህዳር 10/2011 የዘንድሮውን የመልካ ሶር እሬቻ በዓል በተሻለ የህዝብ ተሳትፎ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ሾኖ አስታወቁ፡፡ የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ሾኖ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢሉአባቦር ዞን መቱ ወረዳ በየዓመቱ የሚከበረውን የመልካ ሶር እሬቻ በዓል በመጪው ህዳር 16 ቀን 2011 በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ካለው አንፀባራቂ ለውጥ የተነሳ የዘንድሮ በዓል ካለፉት ዓመታት በተሻለ የህዝብ ተሳትፎ ይከበራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ በዓሉን ስኬታማ ለማድረግ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲያከናውን መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ አባገዳ ከሊፋ እንዳሉት በዓሉ ያለምንም ችግር በሰላምና በድምቀት እንዲከበር ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ቄሮዎች እና ፎሌዎች ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሆን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል፡፡ የመልካ ሶር እሬቻ በዓል በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪውን ለማመስገን እና ፍቅርና አንድነቱን ለማጠናከር የሚያከብረው ዓመታዊ በዓል መሆኑንም አባገዳ ከሊፋ ተናግረዋል፡፡ የኢሉአባቦር ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ በቀለ በበኩላቸው በዓሉ በሰላማዊ ሁኔታ በድምቀት እንዲከበር የዞኑ አስተዳደር የድርሻውን እንደሚወጣ አመልክተዋል፡፡ የዘንድሮው የመልካ ሶር እሬቻ በዓል በአሁኑ ወቅት ከተፈጠረው አስተማማኝ ሰላምና ሀገራዊ ለውጥ የተነሳ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ይከበራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮው የመልካ ሶር እሬቻ በዓል ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የመቱ ከተማ ነዋሪ ወጣት አዲሱ ቡልቲ ነው፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲከበርም ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በኢሉአባቦር ዞን መቱ ወረዳ በየዓመቱ በሚከበረው የመልካ ሶር እሬቻ በዓል ላይ ከምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣ ከኢሉአባቦርና ቡኖ በደሌ ዞኖች የተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ በርካታ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይታወቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም