ኢትዮጵያና አንጎላ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ አቋም አላቸው

77
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 ኢትዮጵያና አንጎላ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው አስታወቁ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአንጎላውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። በዚሁ ጊዜ የአንጎላው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማኑኤል ዶሚንጎስ ኢትዮጵያና አንጎላ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን አንጎላ ከቅኝ አገዛዝ ለመውጣት ባደረገችው እንቅስቃሴ ላይ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። ''ይህን ታሪካዊ ግንኙነት በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ለማጠናከር ምቹ ጊዜ ላይ ነን'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በአገሪቷ እየመጣ ያለውን ለውጥ ያደነቁ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የኢትዮ- ኤርትራ ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ትልቅ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል። ኢትዮጵያና አንጎላ ቡና አምራች ከመሆናቸው ባለፈ ሁለቱም የነዳጅ ሃብት ያላቸው በመሆኑ በጋራ ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉም ተናግረዋል። የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በአገሮቹ ከፍተኛ መሪዎች ደረጃ ግንኙነት መጀመሩን ለዚህ ደግሞ የአንጎላ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አገራቸውን እንዲጎበኙ ጥሪ ማድረጋቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ለአካባቢው አገሮች ሰላምና መረጋጋት እያደረገችው ያለውን ድጋፍ ሚኒስትሩ አድንቀዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያና አንጎላ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አረጋግጠውላቸዋል። በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል ዋና ጸሃፊ ሚካኤል ሲዲቤ ጋር ውይይት አድርገዋል። ዋና ጸሃፊው በኢትዮጵያ የኤድስ ስርጭትን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ስርጭቱ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበትና ይህ ስራ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ብቻ የሚሰራ ሳይሆን የአገር መሪዎችም ተሳትፎ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በአንዳንድ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር አለምአቀፍ አጋሮች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም