አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ልምድ ሊወስዱ ይገባል ተባለ

106
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011  የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ ሊወስዱ እንደሚገባ የአረንጓዴ ልማት ፈንድ ድርጅት ገለጸ። የኢትዮጵያ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር በአየር ንብረት ለውጥና ተግዳሮቶች ዙሪያ የታዳጊ አገራት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። በውይይቱ የ47 አገራት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ስራን ከግብ ለማድረስ አገራቱ የአቅምና የቁርጠኝነት ማነስ እንደሚታይባቸው ተነስቷል። በአረንጓዴ ልማት ፈንድ የግሉ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሚስስ አያን አዳም እንዳሉት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን ቅድሚያ በመስጠት ከሌሎች አገራት ቀድማ ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር የገባች አገር ናት። በተጨማሪም ጠንካራ አስተዳደራዊ ውሳኔ በመስጠት፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በመገንባትና ሴቶችና ህፃናትን የሚጠቅሙ ከአየር ንብረት ጋር የሚጣጣሙ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ረገድ ኢትዮጵያ ልምድ ልታካፍል የምትችል አገር ናት ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ታዳጊ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥና ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የሚፈለገውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘትና ለውጥ ለማምጣት ጠንካራ እቅድና ጥሩ አፈፃፀም ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል። ኢትዮጵያ በዘርፉ የታዳጊ አገራት ህብረት ሰብሳቢ ስትሆን አገራቱ ለሚሰሩት ስራ ከበለጸጉ አገራት የገንዘብ ድጋፍ አግኝተው ለውጥ እንዲያመጡ ከፍተኛ የማስተባበር ሚና እየተወጣች መሆኗን የተናገሩት ደግሞ የህብረቱ ሊቀ-መንበር አቶ ጀንበር እንዳለው ናቸው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ጠንካራ እቅድ የማውጣት፣ ተደራድሮ ገንዘቡ እንዲፀድቅ የማድረግና ዕቅዱን የማስፈፀም ችግር መኖሩን ገልፀዋል። ከአረንጓዴ ልማት ፈንድ በኩልም የአሰራር ግልፅነት ችግሮች እንደሚታዩና ይህ ውይይት ችግሩን ለመፍታት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የአረንጓዴ ልማት ፈንድ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል አገልግሎት የሚውል በአመት 100 ቢሊዮን ዶላር ይሰበስባል ተብሎ ቢታቀድም ላለፉት ሶስት ዓመታት ስምንት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው ከበለፀጉ አገራት መሰብሰብ የቻለው። በአሁኑ ለዚሁ አገልግሎት የሚውልና ለአገራቱ የሚከፋፈል 100 ሚሊዮን ዶላር ለማስፈቀድ የሚደረገው ጥረት በማለቅ ላይ በመሆኑ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የቀሩት ውይይቶች ተደርገው ገንዘቡ እንደሚለቀቅና ወደ ስራ እንደሚገባም ተገልጿል። በመሆኑም አሁን በተጀመረው የአራት ቀን ውይይት ከታዳጊ አገራቱ፣ ከአረንጓዴ ልማት ፈንድና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በኩል ያጋጠሙ ችግሮችን በመወያየት የተሻለ ገቢ ለማግኘትና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የተሻለ ስራ መስራት እንደሚቻል ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም