የከፍተኛ ሌብነትና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች መያዝ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ነው---ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

164
መቀሌ ህዳር 10/2011 በከፍተኛ ሌብነትና ሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ መጠናከር የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ፍላጎት መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። በቁጥጥር ስር የማዋል ስራው አፈጻጸም የህግ ልእልናን በሚያስከብር መልኩ መከናወን እንዳለበትም ምክትል ርዕሰ- መስተዳድሩ አመልክተዋል። ዶክተር ደብረጽዮን ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የትግራይ ህዝብ ለህግ ልእልና መረጋገጥ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለና ጽኑ አቋም ያለው ነው። "የህግ ልእልና ካልተረጋገጠ ግጭት ይሰፍናል" ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፣የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብም ለዚህ የማያዋላዳ አቋም እንዳለው ተናግረዋል። "የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ሌብነትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ብሎ የጠረጠራቸው አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሜቴክና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቶች የጀመረውን ስራ አጠናክሮ በሁሉም ተቋማት ሊቀጥልበት ይገባል"ብለዋል። "የህግ ልእልና የማስከበር ስራው በተወሰኑ ተቋማት መታጠር የለበትም" ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን ክልሎችን ጨምሮ በርካታ የፌዴራል ተቋማት ላይም መሰል ስራዎች መታየት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል። ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉትን አካላት በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ የህግ ልእልናን የሚያረጋግጥ እንጂ የፖሊቲካ መጠቀሚያና ቁማር ሊሆን እንደማይገባ የተናገሩት ዶክተር ደብረጽዮን፣"ችግር ያለበት ሰው መጠየቅ አለበት" ብለዋል። ሁሉም ነገር በመረጃ ላይ መመስረት እንዳለበት ገልጸው ቅጣቱም ሌሎችን የሚያስተምር መሆን እንደሚገባው አስረድተዋል። በጥፋት የተጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ግልጽና ከአድልዎ የጸዳ መሆን እንዳለበትና ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ እንዳይሆን በጥንቃቄ ሊሰራ እንደሚገባውም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አመልክተዋል። በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉት አካላት በመገናኛ ብዙኃን ጥፋተኛና ወንጀለኛ ተደርገው እየቀረቡ መሆኑ የህግ ልእልና ጉዳዮችን ለማጣራትና ለመፍረድ የተቋቋሙትን ፍርድ ቤቶችና የፖሊስ ተቋማት ተግባር ያለአግባብ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይሔም ፍትህን ከማስከበር እሳቤ ጋር የሚጣረስና የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፋ መሆኑን ተናግረው አፈጻጸሙ ህግና ፖለቲካን በማቀላቀል ሳይሆን ሁለቱንም በመለያየት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም