የሰራተኞች መደራጀት ጥቅማቸውንና መብታቸውን ከማስከበር አልፎ ለተቋም ውጤት እያመጣ ይገኛል

272
አዲስ አበባ  ሚያዝያ 23/2010 የባንክና መድህን ሰራተኞች ማህበር ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳን አቶ ደስታ በርሄ ሰራተኞች ከመደራጀታቸው በፊት ጥያቄያቸውን በተበታተነ መልኩ ያቀርቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ጥያቄያቸውም ምላሽ ሳያገኝ መብታቸው ተጥሶ አሰሪ ብቻ የበላይ ሆኖ የሚኖርበት ወቅት እንደነበር ይናገራሉ። የሰራተኞች ማህበር ከተደራጀ ወዲህ ግን ሰራተኞች የሚገባቸውን ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ በማድረግ፤ እያንዳንዱ ሰራተኛ በተናጠል የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች በህብረት ማቅረብ  ተጀምሯል። በተጨማሪም ሰራተኞች በሰሩት ስራ ተመዝነው የሚገባቸውን ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ ከአሰሪው ጋር የጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። በሰራተኛው ዘንድ የስነ ምግባር ችግር ሲኖርም በሰራተኛ ተወካይ አማካኝነት ሰራተኛውን ሲበድል የሚያርምበት ጥሩ ሲሰራ የሚበረታታበት አሰራር መፍጠር ችለዋል። ሰራተኞች ያለአግባብ ከስራቸው ሲፈናቀሉ ጠበቃ ከማቋቋምና ደመወዝ ከመክፈል አንጻርም ማህበራቸው የሚያከናውናቸው ተግባራት እንዳሉ አቶ ደስታ ይጠቁማሉ። መደራጀት ከሰራተኛው በላይ ለአሰሪው እንደሚጠቅም በመጥቀስ "ስንደራጅ በድርጅቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በሰለጠነ አኳኋን በአንድነት ለመፍታት ያስችለናል" የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። እንደ ባንክና መድህን ሰራተኞች ማህበር ኢንዱስትሪ ፌድሬሽን መደራጀታቸው ባንኮችም ሆነ ኢንሹራንሶች ትርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ። የንግድ ቴክኒክና ህትመት ኢንዱስትሪ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ደበሌ በሰጡት አስተያየት በዘርፉ ያሉ ሰራተኞች በመደራጀታቸው በጥቅምና መብታቸው ላይ እንዲደራደሩ አስችሏቸዋል። ከመደራጀታቸው ሰራተኞች መብታቸውን በተናጠል ሲያቀርቡ ተቀባይነት እንዳልነበረውም ጨምረው ገልጸዋል። 'ሰራተኞች ጥያቄያቸውን ተደራጅተው በማቅረብ መብታቸው እየተከበረ በመሆኑ የተረጋጋ የስራ አካባቢ እንዲኖር በማድረግ የተቋማቸውን ስራ ውጤታማ እንዲሆንም እያደረገ ነው' ብለዋል። አሰሪው በማህበር የተደራጀ ሰራተኛ ካለው በተናጠል የሚመጡ ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ እንዲመጡ ያግዘዋል የሚል ሃሳብም አላቸው። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ራሄል አየለ ሴቶች በጨርቃ ጨርቅ፣ አበባ እንዲሁም ቆዳ ኢንዱስትሪ በስራ ላይ መገኘታቸውን በጥሩ ጎኑ ያነሳሉ። በዚሁ ስራ ላይ ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ለሚገኙ ሴቶች የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅና መብቶቻቸው ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። ይህም ህግና ደንብ አውቀው በተደራጀ ሁኔታ መብታቸውን እንዲጠይቁ ማድረግ ያስችላቸዋል ብለዋል። በመሆኑም መደራጀት አንድነትን በመፍጠርና የተበደሉ ሰራተኞች መብት እንዲከበር ከማድረግ አንጻር እገዛ እንዳለው ነው  አስተያየት ሰጪዎች  የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም