ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ምስጋና አቀረቡ

73
አዲስ አበባ ህዳር 9/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ መላው ህዝብና ፖሊስን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት አንዲጠናቀቅ በጋራ በመሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቀረቡ። በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ስብሰባ መጠናቀቅን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ መግለጫቸው በስብሰባው ምክንያት መንገዶች በአንዳንድ ቦታ ሲዘጉ ለተወሰኑ ደቂቃዎች  የትራፊክ መጨናነቅ ነበር፤ አንዳንድ አገራዊ ክዋኔዎችም የቦታ መቀያየር አድርገዋል ሆኖም ህብረተሰቡ ያሳየው ትብብር እንደ ሁልጊዜው "እንግዶቻችን ያስገረመ ነው" ብለዋል። ህዝቡ ይህንን ያደረገው እንግዳ ተቀባይ ድንቅ ህዝብ ከመሆኑም ባሻገር የተቀበለውን እንግዳ በቸር የመሸኘት አገራዊ ኃላፊነት በድርብ የተሰጡት ታላቅ ህዝብ በመሆኑ ጭምር ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው "ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካውያን መዲና ስትሆን የእንግዶቿን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት በሚገባ ትወጣለች የሚል እምነት ተጥሎባት ነው" ብለዋል። ይህንንም ታላቁ ህዝብ፣ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላትና ፖሊስ በጋራ በመሆን አኩሪ በሆነ ትጋትና የመናበብ ትብብራዊ አብሮነት በብቃት የተወጡት መሆኑን አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሰሞኑን እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ የፀጥታው ጥበቃ ጠበቅ ሊል እንደሚችል ህብረተሰቡ ይገነዘባል ተብሎ ይታመናል ሲሉ ገልፀው ህዝብ ለለውጥ ሌት ተቀን እንደሚደክም ሁሉ ለውጡን ለማደናቀፍም ሌት ተቀን የሚደክሙ እኩያን የመኖራቸው ነገር ከማናችንም ቢሆን የተሰወረ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። እንቅፋት ፈጥረው የሀገራችንን ገፅታ እንዲያበላሹ በምንም መልኩ ዕድል ፈንታ አንሰጣቸውም ሲሉም አስገንዘበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታ ኃይሎችን፣ ሆቴሎችን፣ የአየር መንገድ ሰራተኞችን፣ የትራፊክ ፖሊሶችን፣ የአዲሰ አበባ ወጣቶችንና ተማሪዎችን፣ በተለይም ደግሞ የመዲናዋ ነዋሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ መላው ህዝብን "በኢፌዴሪ መንግስት ስም በተለየ አክብሮትና ፍቅር ላመሰግናችሁ አወዳለሁ" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ መግለጫቸው የህብረቱ ስብሰባ የህብረቱን ተልዕኮዎች በብቃት ሊያሳካ በሚችልበት መንገድ ለማደራጀት የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉን መናገራቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል። የአፍሪካ ዋና የለውጥ ኃይል የሆነውን ወጣቱንና አፍሪካን ተሸክመው እዚህ ደረጃ ያደረሷትን ሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ውሳኔዎችም በጉባኤው መተላለፋቸውን አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም