በጫጫ ከተማ በ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ግንባታ ተጀመረ

133
ደብረ ብርሃን ህዳር 9/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ግንባታ መጀመሩን የወረዳው ቴክኒክና ሙያ ኢንተር ፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ወላጆች ኮሌጁ ተማሪዎች ሥልጠናውን በአቅራቢያቸው ለመከታተል ያስችላቸዋል ብለዋል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደፋሩ አሰፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ግንባታው አንጎለላ ጠራ ወረዳ ርዕሰ ከተማ የተጀመረው የኮሌጅ   የአካባቢውን ሕዝብ የረዥም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ ነው። ግንባታው የንድፈ ሐሳብና የተግባር መማሪያዎችን ጨምሮ የቢሮ አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ያካትታል። "የኮሌጁን ግንባታ በ2012 የትምህርት ዘመን በአውቶሞቲቭ፣ በኤሌክትሪክሲቲ፣ በእንጨትና ብረታብረት የሙያ ዘርፎች 150 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን ይጀምራል" ብለዋል። የጫጫ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙላቱ ኃይሉ በሰጡት አስተያየት  ከዚህ ቀደም በአካባቢው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ባለመኖሩ ተማሪዎች ወደ አቅራቢያ ከተሞች ሄደው ለመሰልጠን ይገደዱ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህም ለቀለብና ቤት ኪራይ ወጪና ለእንግልት ይዳረጉ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፣ነዋሪዎች ኮሌጁ እንዲገነባላቸው ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየታቸውን ገልጸዋል። "የኮሌጁ መገንባት 10ኛና 12ኛ ክፍል ካጠናቀቁ በኋላ በቴክኒክና ሙያ ለመሰልጠን የሚፈልጉ ወጣቶች በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስችላል" ብለዋል። በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት 69 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይገኛሉ፡፡                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም