ህጻናትን ከጥቃት ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው-የደቡብ ክልል ህጻናትና እናቶች

71
ሃዋሳ ህዳር 9/2011 ህጻናትን ከጥቃት ለመከላከልና መብታቸውን ለማስከበር ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው የደቡብ ክልል ህጻናትና እናቶች ገለጹ፡፡ ’’ፍቅር ተስፋ ጥበቃ ለሁሉም ህጻናት!’’ በሚል መሪ ቃል ለ13ኛ ጊዜ የዓለም ህጻናት ቀን ከነጭ ሪቫን ቀን በክልል ደረጃ ትናንት በሐዋሳ ከተማ ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የተሳተፉ አንዳንድ ህጻናትና ሴቶች እንደገለጹት በተለይ በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና መብታቸውን ለማስከበር ባለድርሻ አካላት መቀናጀት አለባቸው። የክልሉ ህጻናት ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባዔ ህጻን መታሰቢያ ንጉሤ እንደገለጸችው በየዓመቱ የህጻናት ቀንን ከማክበር ባለፈ ቋሚና ዘላቂ የሆነ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ "ከችግሩ ስፋት አንጻር ጉዳዩ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይሆን፤ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት ሊፈቱት ይገባል" ብላለች ፡፡ "ህጻናትን ለጎዳና የሚዳርጋቸውን ምክንያት መለየትና አስቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል" ያለችው ህጻን መታሰቢያ፣ ፍቅርና ተስፋ በመስጠት የወደፊት ተስፋቸውን ማስመር እንደሚያስፈልግም ተናግራለች፡፡ ከየም ልዩ ወረዳ ህጻናት ፓርላማ የመጣው ህጻን ኤፍሬም ከፈለ በበኩሉ የፍቺ መበራከት የህጻናት መብቶች እንዲሸራረፉ እንደሚያደርግ አመልክቶ፣አብዛኛዎቹ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ህጻናቱን ከግምት እንደማያስገቡ ገልጿል፡፡ በህጻናት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚሰጠው ቅጣት ተመጣጣኝ አለመሆኑንና ህገ- ወጥ የህጻናት ዝውውርን ለመከላከል የሚደረገው ጥረትም በቂ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ "አካል ጉዳተኛ ህጻናትን በፓርላማው በማካተትም አካል ጉዳተኝነት አለመቻል እንዳልሆነ ማሳየት ያስፈልጋል" ብሏል፡፡ በየአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከህጻናቱ ጀምሮ የመንግሥት ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡ "ለአካል ጉዳተኛ ህጻናትና ሴት ተማሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ዝቅተኛ ነው" ያሉት ደግሞ በታቦር ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት መምህርት መስተዋት ጌታቸው ናቸው፡፡ ቢሮው ትምህርቱ በሚሰጥባቸው አምስት ትምህርት ቤቶች በመቀናጀት ችግሩን እንዲፈታው አመላክተዋል፡፡ "አካል ጉዳተኛ ህጻናት ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ በመሆናቸው ማህበረሰቡ ድረስ በመውረድ መብቶቻቸውን ለማስከበር መሥራት ይገባል " ብለዋል ። አካል ጉዳተኛ ልጃቸውን  ይዘው በበዓሉ የታደሙት ወይዘሮ ዝናቧ በኃይሉ በበኩላቸው የልጃቸው አባት በህጻኑ ምክንያት ጥለዋቸው እንደጠፉ ገልጸው፣ የአካል ጉዳተኛ ህጻናት ችግር የእናቶችም ለመሆኑ አንድ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በርካታ እናቶች ለተመሳሳይ ችግር ተጋላጭ በመሆናቸው ቢሮው እስከ መንደር ድረስ በመዝለቅ ችግሩን እንዲመለከትና የግንዛቤና የሙያ ትምህርት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ የደቡብ ክልል ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አጸደ አይዛ "ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዞ በክልሉ ያለው ችግር ሰፊ ቢሆንም፤ ከአደጃጀቶች ጋር በመሆን እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናትን ጨምሮ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በቅርበት እየተሰራ  መሆኑን አመልክተው፣ በዓመት አራት ጊዜ የግምገማ መድረክ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የልጃገረዶች ክበባት ያቋቋሙ ወረዳዎች እንዳሉ የገለጡት ኃላፊዋ፣ "በግርዛት ላይ ያለው ሕጋዊ ቅጣት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጋር በመነጋገር የማስተካከያ ሥራ ተጀምሯል" ብለዋል፡፡ "የህጻናት መብቶችን ለማስከበርና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እስከ ልማት ቡድን በወረደ አደረጃጀት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው ናቸው፡፡ "ከችግሩ ጥልቀት አንጻር የተሰራው ሥራ በቂ ባለመሆኑ መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት፣ ከሃይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ለአካል ጉዳተኛ ሴቶችና ህጻናት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። በበዓሉ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ የሚመለከታቸው አካላትና ህጻናት ተገኝተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም