የተከሰተው የጸጥታ ችግር የሰሊጥ ምርታችንን ለገበያ እንዳናቀርብ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው...በምስራቅ ወለጋ አርሶ አደሮች

85
ነቀምቴ ህዳር 9/2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ የቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የፀጥታ ችግር ለማዕከላዊ ገበያ መቅረብ በሚገባው የሰሊጥ ምርታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አርሶ አደሮች ገለጹ። በምስራቅ ወለጋ ዞን በሳሲጋ ወረዳ የሸንኮራ ቀበሌ አርሶአደር ሒርጳ በኮሬ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት በሰሊጥ ምርት ልማት ተሰማርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሲሆኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ከሽያጩ በሚያገኙት ገቢም የመኖሪያ ቤት በመስራት፣ ወፍጮ በመትከልና ባጃጅ በመግዛት ኑሮአቸውን ማሻሻል እንደቻሉ ነው የገለጹት። ዘንድሮም ምርቱን የበለጠ በማስፋፋት ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት አቅደው አብዛኛውን የእርሻ ማሳቸውን በሰሊጥ ሰብል ቢሸፍኑም በሰላም መደፍረስ ምክንያት ምርታቸውን በአግባቡ መሰብሰበ እንኳ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። "መንግስት የአካባቢውን ሰላም ወደ ቀድሞ ከመለሰ ወቅቱ ካልጠበቀ ዝናብ የተረፈውን ምርታችንን በፍጥነት ሰብስበን ወደ ገበያ የምናቀርብበት እድል ይኖራል" ሲሉም ተናግረዋል። ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር ታከለ ረጋሳ በበኩላቸው ከእዚህ ቀደም በዓመት በአማካይ ከ20 እስከ 30 ኩንታል ሰሊጥ አምርተው ለገበያ በማቅረብ  እስከ 100 ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል። በሚያገኙት ገቢም በሁኬ ከተማ ባለ 50 ቆርቆሮ የመኖሪያ ቤት ለመግዛት መቻላቸውን ተናግረዋል። ዘንድሮ የሰሊጥ ልማቱን በማጠናከር ሞተር ብስክሌትና ባጃጅ ለመግዛት አቅደው ወደ ሥራ ቢገቡም በሰላም እጦት ምክንያት እስካሁን ድረስ ምርታቸውን መሰብሰብ እንዳልቻሉ አስረድተዋል። በአካባቢው በሰሊጥ ንግድ ሥራ ከተሰማሩ ነጋዴዎች መካከል አቶ ደረጀ ረጋሳ በሰጡት አስተያየት ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ከ100 ኩንታል በላይ ሰሊጥ ገዝተው ለማዕከላዊ ገበያ አቅራቢዎች አስረክበው ነበር ። ዘንድሮ ግን ወደ ገበያ የሚወጣ የቅባት እህል ስለሌለ ግብር ለመክፈል ጭምር በሚያስቸግር ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል ። የአርሶአደሮችንና የነጋዴውን ስጋት እንደሚጋሩት የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያደታ ጭምደሳ ናቸው። ከዞኑ ባለፈው ዓመት 6 ሺህ 585 ቶን ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቦ እንደነበር የገለፁት ኃላፊው ዘንድሮ 12 ሺህ 303 ቶን ለማቅረብ ጠንካራ ሥራ ተሰርቶ እንደነበር አስታውሰዋል። አምና እስካሁን በነበረው ተመሳሳይ ወቅት ብቻ 2 ሺህ ቶን ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ተችሎ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ በጸጥታ ችግር ምክንያት እስካሁን ወደገበያ የወጣ ምርት አለመኖሩ ሥጋት እንደሆነ ገልጸዋል። "በዞኑ የተመረተው የቅባት እህል በወቅቱ ተሰብስቦ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ካልቀረበ በአርሶ አደሩና በአገራዊ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል" ሲሉም አቶ ያደታ ተናግረዋል። በምስራቅ ወለጋ ዞን በ2010/2011 የመኽር ወቅት ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቅባት እህል መሸፈኑንና በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች 14 ወረዳዎች የቅባት እህል አብቃይ  መሆናቸው ታውቋል። ኃላፊው እንዳሉት የአካባቢው ሰላም በፍጥነት ከተረጋጋ በዞኑ በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች በ287 የገበያ ማዕከላት ተደራጅተው የሰሊጥ ምርቱን  ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በመጠባበቅ ላይ ናቸው ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም