ኤክስፖውና ዐውደ ርዕዩ አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው የስራ ኃላፊዎች ገለጹ

53
መቀሌ ህዳር 9/2011 በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የፋይናንስ ተቋማት ኤክስፖና ዐውደ ርዕይ አገልግሎቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ገለጹ። በመቀሌ ከተማ በተከፈተው ዝግጅት ከ20 ተቋማት በላይ ተካፍለዋል። የተቋማቱ ኃላፊዎችና ተወካዮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ዝግጅቱ ኅብረተሰቡ የባንኮችን አገልግሎትና አሰራር ለመገንዘብና ተጠቃሚ ለመሆን ያስችለዋል። "ባንኮች በብድር አሰጣጥ የሚከተሉትን መመዘኛዎች እንዲያውቅና በአገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸውን ድርሻ እንዲለይ ያስችለዋል"ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት ሪሶርስ ሞቢላይዜሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ሰዋሰው ናቸው። ዝግጅቱ ኅብረተሰቡ ባንኮች ለኢንቨስትመንት መስፋፋትና ቅልጥፍና እያበረከቱ ያለውን ድርሻ በመገንዘብ በተቋማቱ የመገልገል ፍላጎት  እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል። "ባንኮችም ለደንበኞች እየሰጠን ያለውን  አገልግሎትና የፋይናንስ አቅርቦታችን ምን እንደሚመስል ከደንበኞች አስተያየት የምንቀበልበት መልካም አጋጣሚም ይሆናል" ሲሉም ተናግረዋል። የፀሐይ ኢንሹራንስ የመቀሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ፈትለወርቅ አብርሃ በበኩላቸው "ኩባንያችን አዲስ በመሆኑ ሥራ መጀመራችንና አገልግሎቶቻችንን ለኅብረተሰቡ የምናሳውቅበት መድረክ ይሆናል" ብለዋል። ዝግጅቱ ከደንበኞቻቸው ጋር በይበልጥ እንድንተዋወቅ ያደርገናል የሚል እምነት እንዳላቸው  የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ መድህን ድርጅት የሕይወት ኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ አብርሃ ነጋሲ ናቸው። ተቋሙ የሚሰጣቸውን ከ40 በላይ የኢንሹራንስ ዓይነቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀሙበትም ገልጸዋል። በአቢሲኒያ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቅዱስ ዮሐንስ ዝግጅቱ  የባንኮች የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችላቸውና አጋጣሚውን የአሰራር ለውጥና ማሻሻያ የሚያደርጉባቸውን አስተያየቶችን ከደንበኞች ለማሰባሰብ እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል። ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖና ዐውደ ርዕይ ተቋማቱ ለኅብረተሰቡና ለኢንቨስትመንት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማስተዋወቅና ለማጠናከር ታልሞ የተዘጋጀ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም